ጉዋንዥሁ ዎንዶ ባዮቴክ የተባለ 200 ሚሊዮን የህክምና ቴስት ኪቶችን በዓመት የሚያመርት የቻይና ኩባንያ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብቶ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) የጉዋንዥሁ ዎንዶ ባዮቴክ ኩባንያ ተወካዮችን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው በውይይቱ የፋርማሴዪቲካል ዘርፍ በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ የሚገኝ ዘርፍ መሆኑንና ጠቅሰው፤ ኩባንያው በፍጥነት ወደ ስራ ገብቶ ስራ እንዲጀምር ኮርፖሬሽኑ አፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የቻይናውያን ባለሃብቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ከ40 በላይ ቻይናውን ባለሃብቶች በሙሉ አቅማቸው ስራ ላይ ሲሆኑ በዚህም ከ25ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድልን መፍጠር መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
የኩባንያው ተወካዮች በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በሁለት ምዕራፎች ስራውን እንደሚያከናውን ገልጸው በዚህም ከ15 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ ማቀዱንና ምርቶቹንም ሰፊውን የኢትዮጵያ ገበያ ለማዳረስ ከማቀዳቸው በተጨማሪ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡም ወደ ሌሎቸ የአፍሪካ ሀገራት ለመላክ ማቀዳቸውን በውይይቱ ገልጸዋል፡፡
ጉዋንዥሁ ዎንዶ ባዮቴክ ኩባንያ ከ150 በላይ ሃገራት ምርቱን የሚያቀርብ በጤና ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ እ.ኤ.አ በ1992 የተመሰረተ የቻይና ግዙፍ ኩባንያ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ አመልክቷል፡፡