ከጃፓኑ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተረፉት ግለሰብ የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸነፉ

27 Days Ago 244
ከጃፓኑ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተረፉት ግለሰብ የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸነፉ

እ.ኤ.አ. ነሐሴ 6 ቀን 1945 አሜሪካ በሂሮሺማ ከተማ ላይ የአቶሚክ ቦምብ በመጣሏ ወደ 140,000 የሚጠጉ ሰዎች ተገደሉ።

ከሶስት ቀናት በኋላ ሁለተኛው የአቶሚክ ቦምብ በናጋሳኪ ከተማ ላይ ተጣለ። ከሁለት ሳምንት በኋላ ጃፓን እጅ ሰጠች፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነትም አበቃ።

ታዲያ ከዚህ የሂሮሺማ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተረፉት ቶሺዩኪ ሚማኪ እና ከጥቃቱ የተረፉት ሌሎች ጃፓናውያን ያቋቋሙት "ሂባኩሻ" ማህበር የ2024 የሰላም ኖቤል ሽልማትን አሸንፏል።

ሂባኩሻ የተባለው ይህ ማህበር እ.ኤ.አ. በ1945 በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ከደረሰው የቦምብ ጥቃት የተረፉ ሰዎችን ያቀፈ ማህበር ሲሆን፤ በቶሺዩኪ ሚማኪ ኒዮን ሊቀመንበርነት ይመራ ነበር፡፡

ማህበሩ ዓለምን ከኒውክሌር ጦር መሣሪያ ጥፋት ለመታደግ በተደረገው ጥረት ላበረከተው አስተዋፅኦ በኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ እውቅና አግኝቷል።

የኖቤል ኮሚቴ ሰብሳቢ ጆርገን ዋትን ፍሬድነስ፤ የቶሺዩኪ ሚማኪ ማህበር "ለኒውክሌር እገዳው መመስረት ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል" ብለዋል።

እ.ኤ.አ. በ 1956 የተመሰረተው «ሂባኩሻ» ማህበር ሥራውን የጀመረው የሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ውድመት ከደረሰ ከ10 ዓመታት በኋላ ነው፡፡

ማህበሩ በኒውክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀም ምክንያት ስለደረሰው "አሰቃቂ ጉዳት" እና ስቃይ የተረፉትን ሰዎች ወደ ተለያዩ የአለም ክፍሎች በመላክ ትምህርት ይሰጥ ነበር።

ማህበሩ ከዚህ ቀደም በ2005 በኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ልዩ እውቅና ያገኘበትን ጨምሮ "ብዙ ጊዜ" ለኖቤል ሽልማት እጩ እንደነበር ተጠቅሷል።

የሰላም ኖቤል አሸናፊው ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት ቶሺዩኪ ሚማኪ፤ በኒውክሌር ጦር መሳሪያ ምክንያት የአለምን ሰላም ማስጠበቅ ይቻላል የሚለውን ሃሳብ ተችተዋል።  

ሽልማቱ - ዲፕሎማ፣ የወርቅ ሜዳሊያ እና 1 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፤ በታህሳስ ወር በኦስሎ በሚካሄደው የአልፍሬድ ኖቤል የህልፈተ ህይወት ማስታወሻ ቀን ለማህበሩ የሚሰጥ ይሆናል ሲል ቢቢሲ ኤኤፍፒን ጠቅሶ ዘግቧል።

በናርዶስ አዳነ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top