በአሜሪካ የተገኘው ግዑዝ አካል የሰው ፈጠራ ወይስ የሌላ ዓለም ፍጡራን ሥራ?

1 Mon Ago
በአሜሪካ የተገኘው ግዑዝ አካል የሰው ፈጠራ ወይስ የሌላ ዓለም ፍጡራን ሥራ?

ምድር ላይ በሚሆኑ፣ በሚደረጉ አጀብ በሚያሰኙ የፈጠራ ስራዎች እንደነቃለን:: በተራቀቁ የጦር ጀቶች፣በተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች፣ ተራራ በሚንጡ ታንኮች የታገዘውን የሀገራትን የጦር ሜዳ ላይ የበላይነት እሽቅድምድም አይቶ መገረምንም እንዲሁ የተላመድነው ይመስላል።

የሆነው ሆኖ ግን የሌላ ዓለም ፍጡራን በምድር ላይ አደረጓቸው እየተባሉ የሚነገሩ በጥናት የሚወጡ ጽሑፎች ግን የዓለምን ቀልብ ከየትኛውም ምድራዊ ግኝት በላይ ለረጅም ጊዜ ተቆጣጥረውት ቀጥለዋል።

ከሰሞኑ የወጣው አዲስ መረጃ የጫረው ግርምት ዓለምን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ የላስ ቬጋሱ ሜትሮፖሊታን ፖሊስ ዲፓርትመንት በሰሜኑ የላስቬጋስ ክፍል ጋዝ ፒክ በሚባለው በረሀማ ስፍራ አንድ ሚስጥራዊ ግዑዝ አካል ማግኘታቸው ይፋ አድርገዋል።

መጀመሪያ ክስተቱ እንደተፈጠረ 10 ጫማ ርዝመት ያለውን አንፀባራቂ አካል በማህበራዊ ድረ-ገጽ ሲዘዋወርና ብዙዎችን ሲያነጋግር የነበረ ሲሆን ይህ ግዑዝ አካል በአይነቱ ለየት ያለ አንፀባራቂ የሆነ ገፅታ እንዳለውም ተገልጿል።

በጉዳዩ ላይ የላስቬጋስ ፖሊስ ባወጣው መረጃ የተገኙትን አንፀባራቂ አካላት ምስል አጋርቶ በስፍራው ተራራ የሚወጡ ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስቧል። በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ከመስጠትም ተቆጥቧል።

በአውሮፓዊያኑ 2020 በአሜሪካ ኡታህ ግዛት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ተመሳሳይ ክስተት መፈጠሩንም በማስታወስ እነዚህ አካላት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ላይ እንደተገኙም ተገልጿል።

ከ4 ዓመት በፊት በኡታህ የተገኘው ይህ አንፀባራቂ ግዑዝ አካል ያለምንም መረጃ ደብዛው እንደጠፋም ነው የተነገረው።

እነዚህ አካላት በተለያዩ ስፍራዎች የመገኛቸውን ምስጢር ለማወቅ የሚሰነዘሩት መላምቶችም የአርቲስቶች የፈጠራ ውጤት ነው ከሚል ጀምሮ የሌላ ዓለም ፍጡራን (ኤልያን )የሰሩት ነው እስከሚል ድረስ በሰፊው ሲንሸራሸርም ነበር።

ይህ ግዑዝ አንፀባራቂ አካል ቀደም ሲል በሮማኒያ፣ ካሊፎርኒያ፣ ኒው ሜክሲኮ እና ላስቬጋስ መታየታቸው ሲገለፅ የውሸት እና ሰው ሰራሽ እንደሆኑ ሲነገርም ቆይቷል።

የጥበብ ውጤት እንደሆኑ የሚያምኑ አካላት በዕውቁ የቅርፃ ቅርፅ ባለሞያ ጆን ማክራከን የተሰራ ስለመሆኑ መላምት ያነሳሉ።

ግኝቱን የተለያዩ ሰዎች በተለያየ መንገድ ሲገልፁትም የተስተዋለ ቢሆንም አዲስ የተገኘውን አንፀባራቂ ግዑዝ አካል በጣም የተለየ እና ከዚህ ምድር ያልሆነ በማለትም ማዕረግ አላብሰውታል።

ምስጢሩ እንደቀጠለ 2024ን ዘልቀዋል ይህ በውሉ ያልተጣራ ታሪክ ዛሬም እንደትላንቱ በይሆናል ብቻ ዓለምን እያወዛገበ ይገኛል።

በሶስና ምንዳ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top