ፒያሳን እና አካባቢውን መጎብኘት አንድ ትልቅ የታሪክ መጽሐፍ እንደማንበብ ያህል ነው፦ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት

1 Mon Ago
ፒያሳን እና አካባቢውን መጎብኘት አንድ ትልቅ የታሪክ መጽሐፍ እንደማንበብ ያህል ነው፦ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት

ፒያሳን እና አካባቢውን መጎብኘት አንድ ትልቅ የታሪክ መጽሐፍ እንደማንበብ ያህል ነው ሲል የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ማዕከል ገለጸ። 

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ባሳለፍናቸው ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች የቱሪዝም እንቅስቃሴው ተቀዛቅዞ እንደነበር አንስተዋል። 

በአዲስ አበባ የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት እና ከተማዋን ሳቢ የማድረግ ስራዎች ዘርፉን ለማነቃቃት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል። 

የኮሪደር ልማቱ በውስጡ በርካታ ነገሮችን ያካተተ ነው ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ እያንዳንዱ መንገድ ለእግረኞች እና ለብስክሌተኞች የተመቸ፣ ዳርቻው የተዋበ እንዲሁም ልዩ ልዩ መስህቦች እና የመዝናኛ ሥፍራዎች ያሉት መሆኑን በአብነት አንስተዋል። 

ይህም ቱሪስቶች በከተማዋ ረጅም ጊዜ በመቆየት ቅርሶችን እና ታሪካዊ ቦታዎችን በአግባቡ እንዲያውቁ ከማስቻሉም በላይ ለዜጎች የሥራ እድልን የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። 

የከተማዋ ገፅታ ሳቢ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴውም የተሳለጠ ከሆነ፤ አዲስ አበባን እንደመሸጋገሪያ ለሚጠቀሙ በርካታ ጎብኚዎች ከተማዋን በአጭር ጊዜ የመጎብኘት አጋጣሚ እንደሚፈጠርላቸው ጠቁመዋል። 

"የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና አካባቢውን ብቻ ማስጎብኘት በራሱ የኢትዮጵያን አንድ ትልቅ ታሪክ እንደማሳየት ነው" ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ፒያሳ እና አራት ኪሎን የመሳሰሉ ቦታዎች ለቱሪስት መስህብ፣ ለሀገርም የገቢ ማግኛ እንደሚሆኑ ተናግረዋል። 

የሚታይ አዲስ ነገር ሲኖር ሁሉም ሰው ደስ ይለዋል የሚሉት የኤችቲ የጉዞ ወኪል ባለቤት  ወ/ሮ ሕይወት ተሾመ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ በተሰሩት የልማት ስራዎች ምክንያት ቱሪስቶች ስለ መዲናዋ ብቻ ሳይሆን እና ስለ ኢትዮጵያ ጭምር ጥሩ ምልከታ ይኖራቸዋል ብለዋል። 

ከታሪካዊ ጉብኝት በዘለለ የከተማ ጉብኝት የሚባል የቱሪዝም ንዑስ ዘርፍ ስለመኖሩ ያነሱት ወ/ሮ ሕይወት፤ እንደዚህ ያሉ የልማት ስራዎች የቱሪስት ፍሰቱን ይጨምራሉ ብለዋል። 

ቱሪስቶች በጉብኝታቸው ወቅት የሚያነሷቸው ጥሩ ፎቶዎች ሳይቀሩ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር እንደሚያደርጉት አንስተዋል። 

ብዙ ሐብት እያለን ጥቂት ብቻ የምናሳይ ነበርን የሚሉት ወ/ሮ ሕይወት፤ አሁን ላይ የከተማ ጉብኝትን ለሚመርጡ ቱሪስቶች ብዙ አማራጮች መፈጠራቸው ለሀገር ገቢም፣ ኩራትም መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች የለሙ በመሆናቸው የቱሪስት ካርታን እንደ አዲስ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል። 

በሜሮን ንብረት


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top