ፈረንሳይ በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ ያላትን የወታደር ቁጥር ልትቀንስ ነው ተባለ

1 Mon Ago
ፈረንሳይ በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ ያላትን የወታደር ቁጥር ልትቀንስ ነው ተባለ

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአፍሪካ ያለውን ወታደራዊ ይዞታ ለመገደብ ባወጡት እቅድ መሰረት ፈረንሳይ በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ ያላትን የወታደር ቁጥር ወደ 600 ለመቀነስ ማቀዷ ተገልጿል።

በእቅዱ መሰረት ፈረንሳይ ከሃገራቱ ጋር በሚኖራት ውይይት ቀድመው የተያዙ ወታደራዊ ስፍራዎችን እና ይዞታውን የሚቆጣጠሩ ኃይሎችን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ አቅዳ እየሰራች መሆኑን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ዘግቧል።

የሃገሪቱ ወታደራዊ ምንጮች እንዳስታወቁት ፈረንሳይ በማዕከላዊ አፍሪካ ጋቦን ውስጥ ወደ 100 የሚጠጉ ወታደሮችን ብቻ እንደምታቆይ ተጠቁሟል።

በሴኔጋል እና በሌሎች የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ከ100 በታች የወታደራዊ ቁጥር ይኖራታልም ነው የተባለው።

የወታደሮች ቅነሳ በአካባቢው አጋሮች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ በየጊዜው ሊስፋፋ እንደሚችል ምንጮች ገልፀዋል።

ከጦርነት ተልዕኮ ይልቅ የፈረንሳይ ወታደሮች በሀገራት ጥያቄ መሰረት ለአጋር ሀገራት ስልጠና እና አቅም የመገንባት ስራ ላይ ይሳተፋሉ ነው የተባለው።

ይህ የወታደሮች ቅነሳ የጀመረው እ.ኤ.አ. በየካቲት 2023 የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የፈረንሳይ ወታደሮች በአፍሪካ የሚኖራቸውን “ቅነሳ” ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top