አዲስ አበባ ከነገ ጀምሮ የምታስተናግደው ሌላኛው ትልቅ ጉባዔ

4 Days Ago 326
አዲስ አበባ ከነገ ጀምሮ የምታስተናግደው ሌላኛው ትልቅ ጉባዔ
ኢትዮጵያ እ.አ.አ. በ2024 በደቡብ አፍሪካ፣ ኬፕታውን በተካሄደ ጠቅላላ ዓመታዊ ጉባዔ፣ የአይዲ ፎር አፍሪካ የ2025 ጠቅላላ ዓመታዊ ጉባኤ አዘጋጅ ሀገር ሆና መመረጧ ይታወሳል።
 
አይዲ ፎር አፍሪካ በአፍሪካ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች መፍትሄ በመስጠት ላይ ያተኮረ ብሎም ደህንነቱ የተጠበቀ እና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ተደራሽነትን የሚያረበረታታ ጉባዔ እና ኤክስፖ ነው።
 
በመሆኑም ጉባዔው በአይዲ ፎር አፍሪካ አዘጋጅነት እንዲሁም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት አስተናጋጅነት ከግንቦት 12 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
 
የአስተናጋጅ ሀገር ምርጫው በርካታ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ሰፊ ግምገማ የተካሄደበት ነበር።
 
ኢትዮጵያም እንግዶችን ለማስተናገድ ባላት ዝግጁነት፣ በአፍሪካ ቀዳሚው የአየር መንገድ ባለቤት በመሆኗ፣ በዲጂታል መንገድ የዘመነ ማህበረሰብ ለመፍጠር በምታደርገው ጥረት እና ለ4 ቀናት የሚቆየውን ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ ለማካሄድ በቂ የኮንፈረንስ አገልግሎት መስጫ አቅም እንዳላት ተገምግሞ መመረጥ ችላለች።
 
በጉባኤው ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የዘርፉ ምሁራን፣ የመንግስት ባለስልጣናትና ተጋባዥ እንግዶች ይሳተፉበታል።
 
የአይዲ ፎር አፍሪካ መስራች የሆኑት ጆሴፍ አቲክ (ዶ/ር)፤ "የቀጣዮቹን አስርት ዓመታት ጉዟችንን በተመለከተ የምናካሂደውን ውይይት በኢትዮጵያ ለማካሄድ ማቀዳችን በጣም ደስ አሰኝቶናል" ብለዋል።
 
በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምፀሀይ ጳውሎስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የጉባኤው አስተናጋጅ ሀገር እንደመሆኗ ለውይይት የሚያነሳሳ፣ ፈጠራን የሚያበረታታ እና በዲጂታል የማንነት መስክ የለውጥ መፍትሄዎችን ለማምጣት የሚያስችል መድረክ ለማፍጠር በቆራጥነት ተዘጋጅታለች በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
 
ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ከበርካታ ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች የተካፈሉባቸውን ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2025ን፣ የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም 2025ን እና የኢትዮጵያ ቴክ ኖሎጂ ኤክስፖ 2025ን በተሳካ ሁኔታ ማዘጋጀቷ የሚታወስ ነው።
 
በሴራን ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top