ኢትዮጵያ በዓመት 20 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ ማምረት ጀመረች

2 Days Ago 280
ኢትዮጵያ በዓመት 20 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ ማምረት ጀመረች

በኢትዮጵያ ሲሚንቶ የማምረት አቅምን በዓመት ወደ 20 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማድረስ መቻሉ ተገለፀ።

ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በድሬዳዋ ከተማ የተገነባውን የፓዮኔር ሲሚንቶ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማስፋፊያ ፕሮጀክት መርቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ወቅት፤ በኢትዮጵያ እና በቻይና ባለሃብቶች አጋርነት የተገነባው ፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካ ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፍ አልሚ ባለሃብቶች አጋርነት የዕውቀት ሽግግርና የካፒታል ፍሰትን እንዲሁም ምርታማነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚያስፈልገውን ግብዓት ለማግኘት ጥልፍልፍ መንገዶችን ይጠይቅ እንደነበርም አውስተዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) በበኩላቸው፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለሲሚንቶ ምርት አቅርቦትና ፍላጎት ምላሽ የሚሰጡ እንደ ለሚ ሲሚንቶ ዓይነት ግዙፍ ፋብሪካዎች ተገንብተው ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሲሚንቶ የማምረት አቅምን በዓመት ወደ 20 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማድረስ መቻሉን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ መሰረተ ልማት የምትገነባ ሀገር በመሆኗ የሲሚንቶ ግብዓት ወሳኝ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

አሁን ላይ የነባር ፋብሪካዎችን ምርታማነት በማሳደግና አዳዲሶችን ወደ ስራ በማስገባት ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ለጎረቤት ሀገራት ሲሚንቶ ማቅረብ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አራት የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ወደ ስራ በማስገባት የሲሚንቶ አምራቾችን አቅም የማሳደግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እና ቻይና ባለሃብቶች አጋርነት በአጭር ጊዜ የተገነባው የፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካም ከፍተኛ ጥራት ያለው ምርት በማምረት የኢትዮጵያ አዲስ የስራ ባህል ልምምድ መገለጫ ለመሆን መብቃቱን አስታውቀዋል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top