20ኛው የዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) አህጉራዊ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከዓለም ሥራ ድርጅ በጋራ ያዘጋጁት ይህ ኮንፈረንስ ጤናማ ሥራ እና ምቹ የሥራ ከባቢን የመፍጠር ዓላማ አለው። ይህን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ማጣመርም ሌላኛው ግቡ ነው።
"ጠንካራ ማኅበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው ኮንፈረንሱ፣ መሪ ቃሉን ሰፊ የሥራ ዕድልን መሠረት ካደረገ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም (EIIP) ጋር አስተሳስሯል።
ሰፊ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ መሠረተ ልማት ግንባታ ደኅንነቱን የጠበቀ የሥራ ዕድል በመፍጠር ድህነትን ቀንሶ የአዳጊ ሀገራተን ምጣኔ ሃብት እንደሚያነቃቃ ይታመናል።
ፕሮግራሙ ሥራዎችን ከማሽኖች ይልቅ በርካታ ሰዎችን በማሳተፍ በመሥራት ለሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠርን ያበረታታል።
በተለይ የሰው ኃይል በስፋት በሚገኝባቸው ነገር ግን፣ ሰፊ የሥራ ዕድል በማይገኝባቸው ትናንሽ ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች ይህ አቀራረብ ውጤታማ እንደሆነ የዓለም ሥራ ድርጅት ምሳሌዎችን ይጠቅሳል።
የድርጅቱ መረጃ እንደሚያመለክተው ከ1980ዎቹ ጀምሮ ከ50 በላይ ሀገራት በዚህ መንገድ ተጠቅመው ዘላቂ ዕድገትን አስመዝግበውበታል።
ፕሮግራሙ ፍትሐዊ እና ተመጣጣኝ የሆነ ከፍያ፣ የሥራ ደኅንነት እና ማኅበራዊ ዋስትና እንዲኖር ያደርጋል።
ለሴቶች፣ ለወጣቶች እና ለተጋላጭ ቡድኖች እኩል ዕድል እንዲኖር ያበረታታል። ለዘላቂ ትግበራውም ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ተቋማትን የማጠናከር ሥራም ይሠራል።
መሠረተ ልማቶቹ የሚሠሩለት ማኅበረሰብ በማቀድ፣ በመተግበር እና በጥገና እንዲሳተፍ ያደርጋል። ይህ አቀራረብ የባለቤትነት መንፈስን የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው አካባቢዎች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ የሚያስችል ነው።
የመንገዶች እና መጓጓዣ ፕሮጀክቶች፣ የውኃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች፣ የግድቦች ግንባታ፣ የአረንጓዴ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም ፕሮግራሙ የሚያተኩርባቸው ናቸው። እነዚህም ዘርፎች የሚመረጡት በባሕሪያቸው ሰፊ የሥራ ዕድልን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ነው።
እንደ የዓለም ሥራ ድርጅት መረጃ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ፣ የጤና እና ትምህርት ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያስችላቸው መሠረተ ልማት የላቸውም።
እነዚህን መሠረተ ልማቶችን ማሻሻል እና ጠብቆ ማቆየት የሰዎች የኑሮ ደረጃ መሻሻል ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሊኖረው የሚችል ነው። መሠረተ ልማት የማኅበረሰብን ምርታማነት በመጨመር በገጠር እና በከተሞች ድህነትን መቀነስ እንዲሁም የተሻለ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አቅምን ይፈጥራል።
ፕሮግራሙ መሠረተ ልማትን ከሥራ ፈጠራ፣ ከድህነት ቅነሳ እና ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ዕድገት ጋር ያያይዛል። የውጭ ምንዛሬን ማዳን፣ ከፍተኛ ወጪን መቀነስ፣ ኢንዱስትሪን መደገፍ እና የተቋማትን አቅም ማሳደግም ከፕሮግራሙ ጠቀሜታዎቸ መካከል ናቸው።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ምን እየሠራች ነው?
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ የመንገድ እና የአካባቢ ጥበቃን በመሳሰሉ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች ትገኛለች።
እነዚህ ፕሮጀክቶች አገልግሎቶችን ከማሻሻላቸውም በላይ ሰፊ የሥራ ዕድሎችን እየፈጠሩ ይገኛሉ። በዚህም ወጣቶች፣ ሴቶችን እና ተጋላጭ ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው።
ሀገሪቱ ሰፊ የሥራ ዕድልን መሠረት ያደረገ አቀራረብን ተግባራዊ ያደረገች ሲሆን፣ ፕሮግራሙን ድህነት ቅነሳ እና ሁለንተናዊ ዕድገት ማዕከል ካደረጉ ሀገራዊ ግቦች ጋር በማስማማት ተግባራዊ እያደረገችው ነው።
ከሕዝብ ኢንቨስትመንት ስትራቴጂዎች ጋር በማጣመር ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለኢኮኖሚ ዕድገት ማነቃቂያ እየተጠቀመችም ነው።
እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በሀገሪቱ ውስጥ እየተሠሩ ያሉ የመንገድ መሠረተ ልማቶች፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የኮሪደር ልማት፣ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለዚህ ማሳያዎች ናቸው።
በፕሮግራሙ መሠረት ኢትዮጵያ በእነዚህ ሰፊ የሥራ ዕድል በሚፈጥሩ ፕሮጀክቶች ላይ የተሰማሩ ሠራተኞችን አቅም ግንባታ ሥራም ትሠራለች።
ይህም የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጥራት እና ዘላቂነት ከማሻሻሉም በላይ ሰዎች አቅማቸውን እያሳደጉ ለረጅም ጊዜ ተቀጥረው የሚሠሩበትን አቅም ይሰጣቸዋል። በዚህም በውጭ ባለሙያዎች ይሠሩ የነበሩ ሥራዎችን ጭምር በሀገር ውስጥ የሚሠሩ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ተችሏል።
ኢትዮጵያ ፕሮግራሙን ስትተገብር እንደ አካባቢ ጥበቃ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ ዘላቂ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ላይ ትኩረት ታደርጋለች። እነዚህ እርምጃዎች ሥራን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በማዋሃድ ዘላቂ ዕድገት እና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም እንዲዳብር አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።
ይህ አካሄድ ደግሞ የዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) መርሕ ነው። ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃን ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂም የሥራ ዕድል ላይ ጫና እንዳይፈጥር ፖሊሲ አውጥታ እየተገበረች ትገኛለች።
ይህ ቁርጠኝነቷም ነው ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘውን 20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት የአፍሪካ ጉባኤ እንድታዘጋጅ የተመረጠችው።
በለሚ ታደሰ