በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ ክለቦች መካከል ለመጀመርያ ጊዜ የሚደረግ የፍጻሜ ጨዋታ

9 Hrs Ago 333
በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ ክለቦች መካከል ለመጀመርያ ጊዜ የሚደረግ የፍጻሜ ጨዋታ
እንደ ኦፕታ መረጃ ዛሬ ቼልሲ ከፒኤስጂ የሚገናኙበት የክለቦች ዓለም ዋንጫ ፍጻሜ በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ ክለቦች መካከል ለመጀመርያ ጊዜ የሚደረግ የፍጻሜ ጨዋታ ነው፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ 32 ቡድኖችን ያሳተፈው እና በአዲስ የጨዋታ ቅርጽ የተደረገው የክለቦች ዓለም ዋንጫ ዛሬ ቼልሲ ከፒኤስጂ  በሚያደርጉት ፍጻሜ ይጠናቀቃል፡፡ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሚትላይፍ ስቴዲየም የሚደረገው የዋንጫ ጨዋታም ትልቅ ግምት አግኝቷል፡፡
ሁለቱም ቡድኖች በዚሁ አመት የአውሮፓ ውድድሮችን አሸንፈው የመጡ ናቸው፡፡ ፒኤስጂ የሻምፒዮንስ ሊግ እና ቼልሲ ደግም የኮንፍረንስ ሊግ ዋንጫን አሳክተዋል፡፡
የፈረንሳዩ ሀብታም ክለብ ፒኤስጂ በአመቱ 5ኛ ዋንጫውን ለማሳካት ወደ ሜዳ የሚገባበት ሲሆን በሊጉ 4ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ቼልሲ ደግሞ ያለ ምክንያት ለፍጻሜ እንዳልደረሰ የሚያሳይበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስፔናዊው አሰልጣኝ ሊዩስ ኤነሪኬ በዚህ አመት በ5ቱም የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ያገኟቸውን ታላላቅ ቡድኖች ሁሉም አሸንፈዋል፡፡
ከማድሪድ እስከ ኢንተር ሚላን፣ ከማንችስተር ሲቲ እስከ አርሰናል ከባየር ሙኒክ እስከ ሊቨርፑል እና አትሌቲኮማድሪድ ሁሉንም በማሸነፍ የአውሮፓ ምርጡን ቡድን መገንባታቸውን አሳይተዋል፡፡ የስፔናዊው አሰልጣኝ በወጣት የተገነባው ቡድን በማጥቃቱም በመከለካሉም የተለየ መሆኑ ዛሬ ምሽት ገና በመደረጃት ላይ ለሚገኘው ቼልሲ ትልቅ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በተለይ በኡስማን ዴምቤሌ ዲዘር ዱዌ ኪቪቻ ካቫርስኬሊያ እና ብራድሊ ባርኮላ የሚመራው የአጥቂ ክፍል ለየትኛውም ቡድን አስቸጋሪ መሆኑን ለማሳየት በጥብቅ መከላከል የሚታወቀውን ኢንተር ሚላንን ለዚውም በፍጻሜ ጨዋታ 5 ለ 0 ያሸነፉበትን ብቻ ማስታወስ በቂ ይሆናል፡፡
መሀል ሜዳ ላይ የሁለቱ ወጣት ፖርቹጋላውያን ቪቲናህ እና ጃኦ ኔቬስ እንዲሁም የስፔናዊው ፋቢያን ሪዩዝ ፍጥነት እና የፈጠራ አቅም ሌላኛው የፒኤስጂ አደጋ መፍጠሪ ቦታ ነው፡፡ በእርግጥ በምሽቱ ጨዋታ ቪቲናህ በውድድሩ ድንቅ ጊዜ ካሳለፈው ኢንዞ ፈርናዴዝ ቀላል ፈተና አይጠብቀውም፡፡
አርጀንቲናዊው አማካይ በውድድሩ አንድ ግብ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ 3 ለግብ የሚሆኑ ኳሶች አመቻችቶ አቀብሏል፡፡ በተቃራኒው የዊሊያን ፓቾ እና ሉካስ ሄርናንዴዝን ግልጋሎት በቅጣት የማያገኝው የፒኤስጂ የተከላካይ ክፍል በአዲሱ ፈራሚ ጃኦ ፔድሮ ከሚመራው የቼልሲ የፊት መስመር ትልቅ ፈተና የሚጠብቀው ይሆናል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ለ9ኛ ጊዜ የሚገናኙበትን ጨዋታ እንግሊዛዊው የፊፋ አምባሳደር ሮቢ ዊሊያምስ እና ጣልያናዊቷ የፖፕ አቀንቃኝ ያደምቁታል ተብሎ ይጠበቃል:: የጨዋታው የመጀመርያው 45 አንደተጠናቀቀ የተለያዩ ትርኢቶች እንደሚቀርቡም ፊፋ አሳውቋል፡፡
 
በአንተነህ ሲሳይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top