ለመጀመርያ ጊዜ በአዲስ የጨዋታ ቅርጽ በአሜሪካ ምድር ሲካሄድ የቆየው የክለቦች ዓለም ዋንጫ ነገ ፒኤስጂ ከቼልሲ በሚያደርጉት የፍጻሜ ጨዋታ ይጠናቀቃል።
ተጠባቂው የፍጻሜ ጨዋታ በኒው ጀርሲ 82ሺህ 500 ተመልካቾችን በሚይዘው ሚትላይፍ ስቴዲየም የሚደረግ ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፍጻሜው ጨዋታ እንደሚገኙ ከቀናት በፊት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
የዘ አትሌቲክ ጸሐፊዎች ኤሊያስ ቡርክ እና አዳም ክራፍቶን፥ 45ኛው እና 47ኛውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በፍጻሜ ጨዋታ መገኝትን በተመለከተ ሰፋ ያለ ጽሁፍ አስነብበዋል።
ከሚጠበቁት የእግር ኳስ ከዋክብት በተጨማሪ፤ የዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪው ሰው ትራምፕ በነገው ፍጻሜ የዋንጫ ሥነ ሥርዓት ላይ ከዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጋር እንደሚገኙይፋ ሆኗል።
የፕሬዝደንቱ በፍጻሜው ጨዋታ ላይ መገኝት ከተረጋገጠ በኋላ ከደህንነት ጋር በተገናኝ በርካታ ጉዳዮች እየተነሱም ይገኛሉ።
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ጄዲ ቫንስ በምድብ ጨዋታ ቦርሲያ ዶርትሙንድ ኡስላንን 1 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ ስቴዲየም ተገኝተው ጨዋታውን ተመልክተዋል። በሰዓቱ ለሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ደህንነት የተደረገው ጥብቅ ቁጥጥር ፍጹም የተለየ መሆኑን ጸሐፊዎቹ ገልጸዋል።
በወቅቱ የዶርትሙንዱ አሰልጣኝ ኒኮ ኮቫች ከሆቴል ሲወጡም ስቴዲየም ሲገቡም በአነፍናፊ ወሾች የታገዘ ጥብቅ ፍተሻ መደረጉ ከተገኙት ሰው አንጻር ተገቢ ነው ወይ? የሚል ሃሳባቸውን አጋርተውም ነበር።
በመሆኑም ፕሬዝደንቱ ይገኙበታል ተብሎ በሚጠበቀው የፍጻሜ ጨዋታ፤ የጥበቃው ጉዳይ እጅግ የበለጠ ይጠናከራል ተብሎ እንደሚገመት ዘ አትሌቲክ በሰፊ ሀተታው አስፍሯል።
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ዓመት ሐምሌ 6 ቀን በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በተተኮሰባቸው ጥይት ቀኝ ጆሯቸውን መመታታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ልክ በዓመቱ ሐምሌ 6 ቀን ደግሞ ሀገራቸው ባሰናዳቸው የክለቦች ዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ላይ ይታደማሉ።
የፍጻሜ ጨዋታው የሚደረገው ጥቃቱ በተፈጸመበት ልክ በዓመቱ የመሆኑ ግጥምጥሞሽ ግርምትን የፈጠረ ቢሆንም፤ የአሜሪካ የደህንነት ቢሮ ለነገው ድግስ የተለየ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
ጨዋታው ከሚደረግበት ሚትላይፍ ስቴዲም 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ጀምሮ ጥበቃ እንደሚደረግም ይፋ ሆኗል። ትልልቅ ሰዎች ይገኙበታል ተብሎ በሚጠበቀው ይህ ጨዋታ ላይ፤ ለአደጋ ጊዜ መኪኖች የሚሆኑ መተላለፊያዎች ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ መዘጋጀታቸው ነው የተገለጸው።
ከአካላዊ ቁጥጥር ባሻገር የሳይበር ደህንንት ፍተሻ የሚደረግ ሲሆን ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት፤ በስቴዲየሙ ውስጥ እንደ አደንዛዥ እጽ እና ፈንጂዎች መሰል ነገሮች አለመኖራቸውን በአነፍናፊ ውሾች ጭምር ፍተሻ ይደረጋል ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ በብዙ መልኩ በሚጠበቀው የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ከጂያኒ ኢንፋንቲኖ፣ ከቼልሲ እና ከፒኤስጂ ባለቤቶች እንዲሁም ከኳታሩ ገዥ ታሚም ቢን ሃማድ ጋር እንደሚቀመጡ ይጠበቃል ሲል ዘአትሌቲክ አስነብቧል።
ሰውየው ከተሰነዘረባቸው ጥቃት የተረፉበትን ዕለት እያስታወሱ በግዙፉ ስቴዲየም የሚታደሙበት ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይጀመራል።