የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ኢትዮጵያ ከፍልሰት ጋር በተያያዘ ለምትሠራው ስራ እገዛ ማድረጉን አስታወቀ

2 Mons Ago
የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ኢትዮጵያ ከፍልሰት ጋር በተያያዘ ለምትሠራው ስራ እገዛ ማድረጉን አስታወቀ
የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM)ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን፣ የተመላሽ ዜጎችን ጥበቃና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ለምትሠራው ስራ እገዛ ማድረጉን አስታወቀ።
 
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM) ሪጅናል ዳይሬክተር ራና ጃበር እና በኢትዩጵያ ቺፍ ኦፍ ሚሽን ከሆኑት አቢባቱ ዋኔ ጋር ተወያይቷል።
 
በውይይቱ፤ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከል፣ የተመላሽ ዜጎችን ጥበቃና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።
 
ከነዚህም ተግባራት መካከል መደበኛ ባልሆነ መልኩ ለስደት የተጋለጡ ዜጎችን ወደ አገራቸው ከመጡ በኋላ ወደ መጡበት አካባቢ የመመለስ ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ከምንጩ መካላከል ላይ ያተኮሩ ስራዎች እና ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ምቹ ሀገር እንድትሆን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።
 
ተመላሽ ዜጎች በተለይም ወላጆቻቸውን በስደት ላጡ ህፃናት፣ ሴቶች ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው መልሰው ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ እና ዘላቂ የሆኑ የመጠለያ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ማስፋፋት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አሳስበዋል።
 
በተጨማሪም ሚኒስትሯ ፤መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በኢትዮጵያ እና በዜጎቿ ላይ እያስከተለ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ ለመቀነስ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት( IOM) ካሉ ተቋማት ጋርም በትብብርና በቅንጅት መስራቱንም እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
 
የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት( IOM)ሪጅናል ዳይሬክተር ራና ጃበር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከልና የፍልሰት ተጎጂዎችን በመደገፍና መልሶ በማቋቋም እያደረገች ያለችውን ጥረት አድንቀዋል።
 
ድርጅቱ ኢትዮጵያ የተመላሽ ዜጎችን ጥበቃና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ለምትሠራውን ስራ እገዛ እንደሚያደርግም መግለጻቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top