በዜጎች ላይ እገታና ግድያ በመፈፀም እና የትምህርት ሂደትን በማወክ በመምህራን ላይ በደልና ግፍ እያደረሰ ባለው ፅንፈኛ ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቴ የሱፍ (ዶ/ር) ገለጹ።
በአማራ ክልል ያለውን አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታና በፅንፈኛው ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ በተመለከተ የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ እሸቴ የሱፍ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም፥ ሀገር የማፍረስ ዓላማ ይዞ የተነሳው ፅንፈኛ ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በሰዎች ላይ ግድያ፣ ዘረፋና ውድመት ማስከተሉን አንስተዋል።
ከዚህ ተግባር በመታቀብ ሰላማዊ አማራጭን በመከተል የጥፋት መንገዱን እንዲተው በመንግስት ተደጋጋሚ ጥሪ መቅረቡንና አሁንም የሰላም እጁን እንዳላጠፈ ገልፀዋል።
በዚህም በርካታ ታጣቂዎች የፅንፈኛ ቡድኑን እኩይ አላማ በቅጡ በመረዳትና የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለስ መቻላቸው ይታወቃል።
ከዚህ ውጭ በጥፋት መንገድ በመቀጠል በግድያ፣ ዘረፋና የእገታ ተግባር ላይ በሚገኘው ፅንፈኛ ቡድን ላይ የተቀናጀና የተጠናከረ ህግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።
ዶክተር እሸቴ በማባራሪያቸው ፅንፈኛ ቡድኑ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ መንገድ በመዝጋት የማዳበሪያ አቅርቦትና ሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎቶችን ከማስተጓጎል ባለፈ አርሶ አደሮች እንዳይሰሩና ምርታቸውንም ለገበያ እንዳያቀርቡ ማድረጉን አስታውሰዋል።
የኃይማኖት አባቶችንና የሃገር ሽማግሌዎችን ጭምር በመግደልና በማገት ግፍ ሲፈፅም መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በተለይም በትምህርት ቤቶች ላይ ቦንብ በመጣል፣መምህራንን በማሰርና በመግደል እንዲሁም ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ በመከልከል ፀረ-ህዝብ መሆኑን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
በመሆኑም በዚህ የሀገርና የህዝብ ፀር በሆነ ፅንፈኛ ስብስብ ላይ በጥብቅ ክትትል የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም እየተበታተነ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰዎችን ለመዝረፍና ለማገት እየሞከረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በህዝቡ ትብብር ጥቆማ የፀጥታ ኃይሉ ተከታትሎ እርምጃ እየወሰደበት ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በብዙ አካባቢዎች ሰላም እየተፈጠረ የማዳበሪያና ሌሎች የግብርና ግብአቶች ለአርሶ አደሮች እየቀረቡ መሆኑን ገልፀዋል።
አሁን ላይ እየተወሰደበት ባለው እርምጃ ከመበታተን ባለፈ እርስ በእርሱ ተከፋፍሎ እየተጋደለ ይገኛልም ነው ያሉት።
በህግ ማስከበር እርምጃው እየተበታተነ ያለው ፅንፈኛ ቡድን በተገኘው አጋጣሚ ዘረፋና እገታ እየፈፀመ መሆኑን ጠቅሰው፥ በመከታተል እርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በሁሉም አካባቢዎች በሚደረገው የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ የህዝቡ እገዛ፣ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።