ቤን ኮፍ የቀድሞ የጋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩ ናቸው፡፡ የጋናን ብሄራዊ ቡድን በ1968 የአፍሪካ ዋንጫ አዲስ አበባ ላይ ለፍጻሜ ያደረሱ ሲሆን በዚያ ጨዋታ የተሸነፍነው በአዲስ አበባ አቀማመጥ ነው ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
ስመ ጥሩው የቀድሞ አሰልጣኝ በፊፋ እና በካፍ የተከበሩ ኢንስትራክተር ናቸው፡፡ ህይወታቸው እስኪያልፍ ድረስ በአፍሪካ እና በዓለም እየተዘዋወሩ ብዙ አሰልጣኞችን አስተምረዋል፡፡
እርሳቸው ሲያስተምሩ አንድ የእግር ኳስ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ለመጫወት ሲሄድ ይከብደዋል ሲሉ ይደመጡ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አሰልጣኞችንም ሲያስተምሩ አዲስ አበባ ካላት አቀማመጥ እና የተፈጥሮ ጸጋ አንጻር የትኛውም ቡድን እዚህ ድረስ መጥቶ አሸንፎ መሄድ የለበትም ይላሉ።
“ከባህር ጠለል በላይ 2400 ሜትር ጀምሮ ያለው ከፍታ ከሌላ ሀገር ለሚመጡ ብሄራዊ ቡድኖች እጅግ አስቸጋሪ ነው፤ እናም እሱን እንደ ጥንካሬ ወስዳችሁ ስሩ” የሚል መልእክት ያስተላልፉ እንደ ነበር ይነገራል፡፡ አሁን በህይወት የሌሉት ቤን ኮፍ ይህን የሚሉት ራሳቸው በአሰልጣኝነትም ተቸግረው ስለነበር ነው፡፡ ታድያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዚህ ምን አተረፈ? ከተባለ መልሱ ምንም ነው።
በእርግጥ ከዛሬ 63 አመት በፊት ዋንጫ አንስቷል፡፡ ያኔ ተጠቅሞበት ሊሆን ቢችልም ከዚያ በመለስ ባሉ አመታት ብሄራዊ ቡድኑ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ደጋግሞ ተሸንፏል፡፡የስልጠና መንገዱ እና የጨዋታ ውቅሩ ላይ ስምምነት ስለሌለ ቢያንስ እንደ ተፈጥሯዊ ‘ዶፒንግ’ ሊወሰድ የሚችለውን ጥቅም ገቢር ለማድረግ አልተሞከረም ማለት ይቻላል።
ትንሣኤ የራቀው እግር ኳስ ከወደቀበት እንዲነሳ ተፈጥሮውን ታሳቢ ያደረገ ስትራቴጂ ነድፎ መስራት ይገባል የሚሉት ብዙዎች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንም በዚህ ጉዳይ ደጋግሞ ባለሙያዎችን ጠይቋል፡፡ አሸናፊ ብሄራዊ ቡድን እንዲገነባም ባለሙያዎች ምን ትላላችሁ? በሚል እያንዳንዷ ሀሳብ ተደምራ ውጤት እንድታመጣ አወያይቷል፡፡ ውይይቱም የሚቀጥል ነው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን ላለበት ማንቀላፋት በቀዳሚነት ከተጠያቂዎቹ አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዘግይቶም ቢሆን የነቃ ይመስላል።
እግር ኳሱን ከገጠመው ችግር ለማላቀቅ አንድ ርምጃ ወደፊት የተራመደበትን መድረክ አዘጋጅቷል። ይሄ ደግሞ ይበል የሚያሰኝ ነው። ከታዳጊ ጀምሮ ያሉት ሁሉም ብሄራዊ ቡድኖች የሚመሩበት የሥልጠና መንገድ እና የጨዋታ ውቅርን ለመቅረጽ የቀድሞዎቹን የዋልያውን አሰልጣኞች አሰባስቦ ምን እናድርግ ሲል መክሯል፡፡
ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው፣ ውበቱ አባተ፣ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ፣ ዮሀንስ ሳህሌ፣ ስዩም ከበደ፣ ገብረመድህን ሃይሌ፣ መሳይ ተፈሪ፣ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ አማካሪ አምሳሉ ፈንታሁን እና የፊፋ ታዳጊዎች ልማት ባለሙያ ኢያሱ መርሃጽድቅ (ዶ/ር) በአንድ ላይ በአንድ አዳራሽ ተገናኝተው መምከራቸው እና ምን ይደረግ ለሚለው የየራሳቸውን ሀሳብ ማንፀባረቃቸው ትልቅ እርምጃ ነው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመፍጠር የያዘው ርዕይ እንዲሳካ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን ከታዳጊዎች እስከ ብሄራዊ ቡድን ድረስ ወጥ የሆነ የሥልጠና እና የጨዋታ መንገድን ስራ ላይ ለማዋል አልሟል፡፡ ህልሙንም እውን ለማድረግ ጉዞ ጀምሯል፡፡ ሰነድም እያዘጋጀ ነው፡፡
ስለ ኢትዮጵያ የመከሩት ባለሙያዎች የየራሳቸው የሆነ በጎ ተጽእኖ ያላቸው መሆናቸው ደግሞ ጅምሩ ተስፋ እንዲኖረው የሚያደርግ ይሆናል።
ከእነሱ ሀሳብ የሚቀዳውን ከአሁናዊው የስልጠና አካሄድ ጋር በማዳመር መፍጠር እና መሞከር ጥሩ ነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ግራና ቀኝ ዘመም አመለካከት ያላቸው ሰዎች ሀሳባቸውን አዋጥተው በልዩነት ውስጥ አንድ ሆነው ሃላፊነቱን ለሚረከብ አሰልጣኝ ድጋፍ ቢያደርጉ ለውጥ ይመጣል፡፡
በጋራ የጸደቀ፣ በጋራ የተስማሙበት ነገር አንድ እርምጃ ወደፊት ያደርሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አልፎ አልፎ የሚያስመዘግባቸው ድሎች የመጡበትን መንገድ ማየት፣ ከኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ የሚቀዱ እሳቤዎች፣ የአልሸነፍ ባይነትን መንፈስ እንዴት በጨዋታ መንገድ ውስጥ እናካተው ብሎ ማሰብም አትራፊ ያደርጋል፡፡
የስፖርት ስነ ልቦና ጨዋታን በማሸነፍ ሂደት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ስላለው፡፡ የቀደሙት ባለሙያዎች ሀሳብ እንዲያዋጡ መደረጋቸው ማለፊያ ነው፡፡ ሀሳቡ ምሉዕ እንዲሆን ግን ሌሎች አካላትንም ማካተት ደግሞ የበለጠ ጥሩ ይሆናል፡፡ ወጣት አሰልጣኞች፣ ሁሉንም ኢንስትራክተሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን፣ የስፖርት አካዳሚ ባለሙያዎችን፣ የራሳችን የጨዋታ እሳቤ አለን የሚሉትን እንዲሁም የስፖርት ጋዜጠኞችንም እየጠሩ ማወያየትና ያንን ጨምቆ መውሰድም የተሻለ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ የስልጠና አካዳሚን ማሰብ የመንግስት ስራ ይሆናል፡፡
ለጊዜው ግን ቢያንስ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን እንዴት እንገንባ በሚል የሀሳብ ልዩነት ያላቸውን ልሂቃንን ፌዴሬሽኑ በአንድ አዳራሽ አስቀምጦ ማወያየቱ ለችግሮቹ መፍትሄ እንደ አንድ እርምጃ የሚቆጠር ነው፡፡
ከራስ ባህልና ታሪክ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ፀጋ ጋር የተዛመደ ሳይንሳዊ የስልጠና መንገድ እና የጨዋታ ውቅር ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሸናፊነት!
በሀብታሙ ካሴ