እንደ በዓል ሰሞን ገበያ ማጠናቀቂያው ላይ ግርግር የማያጣው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

8 Hrs Ago 912
እንደ በዓል ሰሞን ገበያ ማጠናቀቂያው ላይ ግርግር የማያጣው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

የ2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሊጠናቀቅ አንድ ጨዋታ እስኪቀረው ድረስ ሻምፒዮኑም አንደኛው ወራጅም ያልተለየበት አመት ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ ለሻምፒዮንነት ድሬዳዋ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ በሊጉ መቆየታቸውን ለማረጋገጥ የሚጠብቁት ቀን፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በመጨረሻው ሳምንት በሚደረጉት ጨዋታዎች የሚመዘገበው ውጤት ካለው ትርጉም አንጻር ፍትሀዊ እንዲሆን ለማድረግ ቅድመ ጥንቃቄ አድርጌአለሁ ብሏል፡፡ ሁለቱ የአዲስ አበባ ከተማ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሻምፒዮንነት እና አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ላለመውረድ የተገናኙበትን እና በተመሳሳይ ፋሲል ከነማ ዋጫውን ለማንሳት እና ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ለመቆየት የተገናኙባቸውን መርሀ ግብሮች በተመሳሳይ ሰአት የተደረጉ ቢሆኑም ፍጻሜው ግን ከውዝግብም ከቅሬታም ያመለጠ አልነበረም፡፡

የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ዕድል ያላቸው ፈረሰኞቹ አዲስ አበባ ከተማን 4 ለ 0 አሸንፈው ዋንጫውን አነሱ፡፡ በራሱ ውጤት በሊጉ መቆየቱን ማረጋገጥ ያልቻለው አዲስ አበባ ከተማ የድሬዳዋን መሸነፍ ከመጠበቅ ውጭ አማረጭ አልነበረውም፡፡ የሊጉን ዋንጫ በተከታታይ ለማንሳት የቅዱስ ጊዮርጊስን መሸነፍ ወይም ነጥብ መጣል የሚጠብቀው ፋሲል ከነማ እስከ 76ኛው ደቂቃ ድረስ ድሬዳዋ ከተማን 2 ለ 0 ሲመራ ቢቆይም በመጨረሻዎቹ 14 ደቂቃዎች በተቆጠሩበት ሶስት ግቦች ተሸነፈ፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ መትረፉን ሲያረጋግጥ ተሸንፎም የመቆየት ዕድል የነበረው አዲስ አበባ ከተማ በመጣበት አመት ወደ ከፍተኛ ሊግ ተመለሰ፡፡

ከዚህ ክስተት በኋላ ሆን ተብሎ የውጤት ማጭበርበር ተፈጽሟል ያሉት የአዲስአበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የስራ ሃላፊዎች ጉዳዮን ወደ ካፍ፣ ፊፋ እና የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት እንወስደዋለን በሚል መግለጫ ሰጡ፡፡ ከጨዋታው በፊት ጭምር ድርድሮች እንደነበሩ በቂ ማስረጃ እንዳላቸው ቢገልጹም ነገሩ ግን አንዳች መዳረሻ ሳያገኝ ባለበት ቆመ፡፡

ይሄንን ለማሳያ ያከል አነሳን እንጂ በተለያዩ ጊዜዎች የመጨረሻዎቹ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በተለያየ ወገን ቅሬታ የሚነሳባቸው ሆነው ያለፉ ባርካታ አጋጣሚዎችን ማስታወስ ይቻላል፡፡ እንዲህ አይነት ቅሬታና ውዝግብ በየትኛውም አለም ያለ ቢሆንም የዚህን ሀገር ለየት የሚያደርገው የተነሳው ውዝግብ እውነትም ይሁን አይሁን የሚያረጋግጥ ገለልተኛ ተቋም አለመኖሩ እና በአወዳዳሪው አካልም ይሁን ጥያቄ ባላቸው ክለቦች በኩል አንዳች መፍትሄ ሳያገኝ ሌላም ጊዜ የሚደገም መሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሰራር አለም ከሚጓዝበት በተቃራኒ የቆመ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው። 

ግን ለምን?

በ2017 የውድድር አመት ከሊጉ መጠናቀቅ ማግስት የተነሳው ቅሬታ ካባለፉት አመታት የተለየ ቢሆንም ግን አሁንም የሊጉ መጨረሻ ውዝግብ ውስጥ እንዲቆይ ያደረገው ነው፡፡ የአንድን ሀገር የእግር ኳስ ሊግ ጠንካራ የሚያሰኘው በቅድሚያ ክለቦቹ ራሳቸው በመቀጥል ሊጉን የሚያስተዳድረው አካል ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ከተመለከትነው በተለይ ክለቦች በመርህ ወይም በአላማ መጓዝ ላይ ሰፊ ችግሮች ያሉባቸው ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

በእርግጥ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ሊጉን የማሰተዳደር ሃላፊነቱን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከወሰደ በኋላ ባለፉት አምስት አመታት ለውጦችን ተመልክተናል፡፡ በዋናነት ሊጉ የቱንም ያክል የጥራት ደረጃው ዝቅተኛ ቢሆንም አለም አቀፍ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንዲያገኝ እና ተደራሽነቱን እንዲያሰፋ የተሰራው ስራ ቀዳሚው ነው፡፡

በዚሁ ምክንያት ተጫዋቾች ራሳቸውን እንዲያሳዩ ዕድል ያገኙበት፣ አለም ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ እንዲውቅ፣ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጀምር እና እንዲጠናቀቀ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከአሁን በፊት አመቱ ሲጠናቀቀ አንዳች ገንዘብ የማያገኙት ክለቦች ከሊጉ ሽያጭ እንደየደረጃቸው ገንዘብ እንዲያገኙም አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሀገራት ሊጎች ካለቡት ደረጃ እና ከሚተዳደሩበት ደንብ አንጻር በጣም በርካታ ነገሮች የሚቀሩት ገና በዳዴ ላይ ያለ ቢሆንም ጅምሮቹን ግን አለማድነቅ አይቻልም፡፡

በተለይ የክለቦች የገንዘብ አስተዳደር ለረጅም ጊዜ መፍትሄ ያላገኝ ጉዳይ ነው፡፡ የክለቦች አመታዊ ወጭ፣ ተጫዋቾችን የሚያስፍርሙበት መንገድ እና የሚሰጧቸው ውል ጭምር ስርአት የለሽ ሆኖ የቀጠለ መሆኑን ራሱ የሊግ አክሲዮን ማህበሩ ከወራት በፊት በሰጠው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡

የበርካታ ክለቦች የገንዘብ ምንጭ መንግስት በሆነበት ሀገር ገንዘቡ የት እንደሚገባ፣ ለየትኛው የእግር ኳስ መሰረተ ልማት እንደዋለ፣ ለየትኛው ተጫዋች ምን ያክል ገንዘብ እንደተከፈለው፣ የውሉ ሁኔታ፣ የምልመላ ጉዳይ፣ የተጫዋቹ መምጣት በክለቡ ላይ የሚያመጣው ለውጥ እና ሌሎች ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን ለእግር ኳሱ መሞትም መነሳትም ምክያት ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች አሁንም ድረስ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተዘነጉ ናቸው፡፡

በተለይ በክለቦች መካከል እየተፈጠረ የመጣው ቅጥ ያጣ ፉክክር የእነሱ ባልሆነ ገንዘብ እንደፈለጉ ተጫዋች የሚያስፈርሙበት ሁኔታ የኢትጵያ እግር ኳስ ፍጹም ጤነኛ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ የሊጉ አክሲዮን ማህበር ዘግይቶም ቢሆን ባለፈው አመት የክለቦች የገንዘብ አስተዳደር መመሪያ አውጥቶ ወደ ትግበራ ቢገባም መቋጫው ግን ውዝግብ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ መድን ሻምፒዮን በሆነበት 2017 ዓ.ም እስከ አሁን ድረስ አክሲዮን ማህበሩም ይሁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በይፋ ወራጅ ክለቦችን አላሳወቁም፡፡ በዕርግጥ በደረጃ ሰንጠረጁ መሰረት አዳማ ከተማ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ስሁል ሽረ ወራጅ ክለቦች ናቸው፡፡ የተጠቀሱት ክለቦችም "የውድድር አመቱ ፍትሀዊ አየደለም የተጣሰ ህግ አለ" በሚል ከሊጉ መውረዳቸውን እንዳልተቀበሉ እና ለጉዳዩ መልስ እንደሚጠብቁ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

ለመሆኑ የክለቦቹ ጥያቄ ምንድን ነው?


አመቱ ሲጀመር ሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ተማምነው ያወጡትን የክፍያ መመሪያ የጣሱትም ራሳቸው ሆነው መገኘታቸው የቅሬታው መነሻ ሆኖ ተቀምጧል፡፡


የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የክፍያ ስርአት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1/2016 የክለቦችን ቀጣይነትና ህልውና ማስጠበቅ የሚችል ስርዓት መፍጠር እና በክለቦች እንዲሁም በተጫዋቾች ለሌላ ሦስተኛ ወገን የሚፈፀሙ ያልተገቡ ክፍያዎችን ማስቆም አላማ አድርጎ የተዘጋጀነው፡፡ መመሪያው ከትንሹ የገንዘብ ቅጣት እስከ ትልቁ ክለቦችን ወደ ታችኛው የሊግ እርከን እስከ ማውረድ የሚደርስ ቅጣትን የያዘ ሆኖ ተቀምጧል፡፡


ዋናው የመመሪያው ማሰሪያ አንድ ክለብ በአመት ለደመወዝ ብቻ ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማድረግ አይችልም የሚለው ነው፡፡
አክሲዮን ማህበሩ ባቋቋመው ገለልተኛ ኮሚቴ በኩል አደረኩ ባለው ማጣሪያ የውድድር አመቱ አጋማሽ ላይ 4 ክለቦች የክፍያ ስርአቱን መመሪያ ጥሰው መገኘታቸውን ከማሳወቅ ባለፈ ቅጣት አስተላልፎ እንደነበርም ይታወሳል፡፡

ነገር ግን በወቅቱ የተቀጡት ክለቦች ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ ውሳኔው ታግዶ እንዲቆይ አድርገዋል፡፡ ቅጣቱ ተፈጻሚ አልሆነም ህግ የጣሱ ክለቦች በዝምታ ታልፈው የውድድር አመቱን አጠናቀዋል በሚል የሊጉ ግርጌ ላይ ያሉ ክለቦች ጉዳዩን እስከ ፊፋ ድረስ እንደሚወስዱት አሳውቀዋል፡፡

ነገሩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት መውሰዱ በራሱ የእግር ኳስ ጉዳዮች ከሚታዩበት አለም አቀፍ አሰራር አንጻር ስህተት መሆኑ በዚህ አመት በሊጉ የተፈጠረውን ነገር መስመር ለማስያዝ ብዙ ጊዜ የሚወስድ ሊያደርገው ይችላል፡፡

በሌላ ኩል እንዲህ አይነት የስፖርት ጉዳዮች መፍትሄ የሚያገኙት እንደ ስፖርቶቹ አይነት ከሀገር ውስጥ ጀምሮ እስከ አለም አቀፍ በተዘረጋላቸው የፍትህ ስርአት እንጂ የ3ኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ካለ ከክለቦቹ ባሻገር ሀገርንም ሊያስቀጣ ስለሚችል ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑ መሰመር አለበት፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ቅጣቱ ተጥሎባቸው የነበሩት መቻል፣ ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት የወሰዱትን የክስ ጉዳይ በአስቸኳይ እንዲያነሱ ያሳወቀው፡፡

ህግ የጣሱ ክለቦች ባሉበት ህግ ያከበርነው ተጎድተናል የሚሉት እንደ መቐለ 70 እንደርታ እና አዳማ ከተማ አይነት ክለቦች ለእግር ኳስ ፌደሬሽኑም ለአክሲዮን ማህበሩም ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ህግ አክብሮ መስራት በሊጉ ዝቅተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ምክንያት አይሆንም፡፡ ለዚህ ማሳያው ምንም አይነት የመመሪያ ጥሰት ያልፈጸሙ ክለቦች ጠንካራ ተፎካካሪ ከመሆን እስከ ሻምፒዮንነት ደርሰዋል፡፡ እንደዚያም ቢሆን ግን ህግ ከጣሱት ጋር በእኩል ሜዳ መወዳደር የለብንም ብለው ጥያቄ ማንሳታቸው ተገቢ ይሆናል፡፡

ብቻ ከአዲሱ መመሪያ አተገባባር ጋር ፈተና የገጠማቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን እና አክሲዮን ማህበሩ ለተነሳባቸው ጥያቄ በቂ መልስ ይሰጣሉ ወይስ እንደ ባለፉት አመታት የክለቦቹ ጥያቄዎች ጥያቄ ብቻ ሆነው ይቀራሉ? መጭዎቹ ቀናቶች መልስ የሚሰጡ ይሆናል፡፡

በአንተነህ ሲሳይ 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top