ተፈጥሮ በፍቅር ገዝታው ቶዮታ ኩባንያን ያስለቀቀችው - ሹብሄንዱ ሻርማ

19 Hrs Ago 293
ተፈጥሮ በፍቅር ገዝታው ቶዮታ ኩባንያን ያስለቀቀችው - ሹብሄንዱ ሻርማ

ለተፈጥሮ ባለው ፍቅር ራሱን ከመኪና መገጣጠም ወደ የደን ባለሙያነት የቀየረው ሻርማ፣ "ሚያዋኪ" የተባለ የተለየ ዘዴን በመፍጠር ክብረ-ወሰን የያዘ የደን ልማት ሥራ እየሠራ ነው።

"ሚያዋኪ" የተባለው የእርሱ ዘዴ ዘመናት የሚወስደውን ሀገር በቀል ጥቅጥቅ ደኖችን በከተሞች እና በተራቆቱ አካባቢዎች በመፍጠር ረገድ በሰፊው የሚታወቅ ሆኗል።

በሕንድ በሚገኙ አምስት ከተሞች ውስጥ ከ17 የሚበልጡ የተፈጥሮ ደኖችን የፈጠረ ሲሆን፣ ደኖቹም ከ105 ሺህ ስኩዌር ሜትር በላይ ስፋት እና ከ36 ሺህ በላይ ዛፎችም አሏቸው።

እሱ የፈጠራቸው ደኖች በዓመት ከ4 ሺህ ኪሎግራም በላይ ካርቦን የሚሰበስቡ ሲሆን ይህም የአየር መበከልን ለመከላከል የራሱን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ማሳያ ነው።

ሹብሄንዱ ሻርማ ከ2 እስከ 4 ዲግሪ ሴልሺየስ ሙቀት በመቀነስ፣ የከርሰ ምድር ውኃን በማሳደግ እና የብዝኃ ሕይወት ሚዛንን በመጠበቅ ከግለሰብ በላይ የሆነ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።

 

በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ደን እንደሚመነጠር በአንጻሩ ደግሞ በርካታ መኪኖች ደግሞ እንደሚመረቱ የሚናገረው የተፈጥሮ ወዳጁ፤ ይህ አካሄድ ከቀጠለ መተንፈሻችንን እናጣለን ይላል።

"ሚያዋኪ" የሚባለውን የደን ልማት ሥራውን እንዴት እንደጀመረ ሲያስታውስ፣ "በ2008 ለቶዮታ ኩባንያ ስሠራ ከዶክተር አኪራ ሚያዋኪ ጋር ተገናኝቼ ነበር፤ በደን ላይ የሠራቸውን የሥራውን ፎቶዎች ስመለከት በጣም ተገረምኩ" ይላል።

ስለ ዛፎችና ምንነት እና ውበት የተማረው ከዶክተር ማያዋኪ እንደሆነ የሚያወሳው ሻርማ፣ በተለይም ሀገር በቀል ዛፎች ያላቸውን ውበት እና የሰዎች እጅ ባይበዛባቸው እንዴት ማደግ እንደሚችሉ መረዳቱን ይናገራል።

ከዶክተር ማያዋኪ የተማረው ሀገር በቀል ዛፎች ለማልማት የተከለሉ አካባቢዎች መለየት እና እርስ በእርሳቸው ተመጋግበው በፍጥነት የሚያድጉ ችግኞችን ለይቶ በአንድ ላይ መትከልን ነው።

ይህ አሠራር የሚተከሉ ችግኞች እንዲደጋገፉ የሚያስችል መሆኑን እና በዚህም ምክንያት የሚተከሉት ችግኞች ከተለመደው በአሥር እጥፍ በፍጥነት እንዲያድጉ፣ በ30 እጥፍ ጥቅጥቅ ደን እንዲሆኑ እና መቶ በመቶ ብዝኃ ሕይወትን ጠቅልለው እንዲይዙ እንደሚያደርጋቸውም ያወሳል።

 

ዶክተር ማያዋኪን ካገኛቸው ከሰባት ወራት በኋላ በቶዮታ ፋብሪካ ውስጥ በዚህ ዘዴ ችግኞችን መትከላቸውን እና በአንድ ዓመት ተኩል ደን ሲሆን ማየቱን የሚያስታውሰው ሻርማ፤ ይህም የማያዋኪን የደን ቡድን በፈቃደኝነት ለማገልገል እና በሂደትም የራሱን ደን ለመፍጠር እንዳነሳሳው ይናገራል።

ከቤተሰቡ እና ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በመጀመሪያው ዙር በ70 ስኩዌር ሜትር ላይ የተከላቸው ችግኞች ከ2 እስከ 3 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ መቶ በመቶ ራሳቸውን መቻላቸውን ይናገራል።

በሕንድም ሆነ በአውሮፓ የተመለከታቸው ደኖች ሀገር በቀል ዛፎችን ከውጭ ከመጡ ዛፎች ጋር ተቀላቅለው መተከላቸውን የሚያወሳው ሻርማ፣ ይህ ደግሞ መጤዎቹ ዛፎች ሀገር በቀሎቹን በሂደት እንዲያጠፏቸው ማድረጋቸውን ይናገራል።

ሻርማ በርካታ ተከታዮችን እያፈራም ይገኛል። በዚህም መሰረት የባንጋሎር ረዳት ኮሚሽነር በወንጀል ምርመራ ተቋማቸው ወስጥ ደን እንዲፈጥሩ ያደረገ ሲሆን፣ የትምህርት ተቋማት እና ሌሎች ሕዝባዊ ተቋማት ውስጥ ወርክሾፖችን በማዘጋጀት በርካቶች የእርሱን መንገድ እንዲከተሉ አድርጓል።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top