"ጋዜጠኛ ወገን የለውም፤ ሃይማኖት የለውም፤ የሚደግፈው ፖለቲካ የለውም …" የሚሉ የጋዜጠኝነት መርሆች አሉ፡፡
እነዚህ መርሆች ግን ምንድን ናቸው? ለመሆኑ ጋዜጠኛ በእነዚህ መርሆች ሲመራ ዜግነቱን ያጣል? ይህ ጉዳይ ከብሔራዊ ጥቅም ጋርስ እንዴት ይናበባል?
የዚህ ሀሳብ መነሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ያነሱት ጉዳይ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "ጋዜጠኝነት ዜግነት የለውም ብላችሁ የምታስቡ ሰዎች ካላችሁ ተሳስታችኋል፤ ጋዜጠኝነት ዜግነት አለው፤ ልክ እንደወታደር፣ ልክ እንደ ሐኪም፣ ልክ እንደ መምህር፣ ልክ እንደ ደኅንነት ሠራተኛ ጋዜጠኝነት ዜግነት አለው፤ ጋዜጠኝነት ብሔራዊ ጥቅም አለው፤ ጋዜጠኝነት የሚቆምለት ሀገር እና ባህል አለው፤ …" ብለዋል፡፡
የጋዜጠኝነት ሳይንስ ውስጥ ስለ ጋዜጠኛ ዜግነት እና የጋዜጠኝነት መርሆዎች "በነቃ ማኅበረሰብ ውስጥ የጋዜጠኛ ዜግነት እና የጋዜጠኝነት መርሆዎች ሁለት ተያያዥ ግን ልዩ ልዩ ፅንሰ-ሀሳቦች ናቸው በሚል" በጥቅል ተጠቅሷል፡፡ ይህም ሲዘረዘር፡-
ጋዜጠኝነት እንደ ሙያ ለጋዜጠኛው የሚሰጣቸው መብቶች ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት፣ መረጃ የማግኘት መብት እና በነፃነት የመንቀሳቀስ መብቶችን የሚያጠቃልል ነው፡፡
እነዚህ የጋዜጠኛው መብቶች ደግሞ የሀገር ሕጎን ማክበር፣ የሀገር ብሔራዊ ጥቀምን ማስጠበቅ እና የሀገር ሰላምን የሚያደፈርሱ ድርጊቶች ላይ አለመሳተፍ ከሚሉት የዜግነት ግዴታዎች ጋር ፈጽሞ የሚጋጩ እንዳይደሉ ነው ጋዜጠኝነትን በተመለከቱ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች እና ስምምነቶች ላይ የሰፈረው፡፡
አንድ ጋዜጠኛ በአንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሀገሮች ዜግነት ሊኖረው ቢችልም እንኳን እውነተኛ የጋዜጠኝነት ጽኑ አቋሙ ግን በእውነት፣ በኃላፊነት እና በሕዝብ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ ታማኝነትን የሚያካትት መሆኑን አሜሪካ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ሚዲያዎች ውስጥ የሠራችው ሳራ ሊ ትግልጻለች።
ጋዜጠኛው እንደዜጋ የሥራው መነሻ እና ማኅበረሰባዊ ይዘቶች ሲሆኑ፣ ዓላማውም በእውቀት እና መረጃ ላይ የተመሰረተ ንቁ ማኅብሰብን መገንባት ነው።
የጋዜጠኝነት መርሆች ደግሞ የነቃ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ተዓማኒነት ያለው እና ከሕዝብ ጥቅም የማይቃረኑ እንዲሁም ጉዳት የማያስከትሉ መረጃዎችን ለማኅበረሰቡ ማቅረብን የሚደነግጉ ናቸው።
የጋዜጠኛው የዜግነት ቁርጠኝነት ከሙያቸው በስተጀርባ ያለው የመነሻ ኃይል ሲሆን፣ የጋዜጠኝነትን መርሆዎችን በተለይም ሀቀኝነትን እና ነፃነትን ተከትሎ ነገር ግን የግል እምነቶችን ከሙያ ውጤት በመለየት ሥርዓት ያለው አቀራረብ ከጋዜጠኛው ይጠበቃል።
የነቃ እና ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብን ለመፍጠር የማያቋርጥ ሚዛናዊነት እና የሕዝብ አመኔታ ያላቸው ዘገባዎችን እና ፕሮግራሞችን ማቅረብ የጋዜጠኝነት ዋናው መርህ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ አንድ ምርጥ ዜጋ ለማኅበረሰቡ የሚያበረክተው ስጦታ ነው።
የቀድሞው የሲኤን ኤን ቴሌቪዢን አዘጋጅ እና ጋዜጠኛ የነበረው ኒክ ቶሶ እንደሚለው ጋዜጠኛ አስፈላጊ የሆኑ ዴሞክራሲያዊ ተግባራትን በመፈፀም የዜግነት ግዴታውን ይወጣል፡፡
እንደዚህ ዓይነቱ ጋዜጠኛ በአስፈጻሚ አካላት የሚፈጸመውን ሙስና የማጋለጥ፣ ስለ ምርጫ ጠለቅ ያለ ትንታኔ በመስጠት፣ የማኅበረሰቡን መልካም እሴቶች የሚያጎሉ ሥራዎችን በመሥራት የሰለጠነ ማኅበረሰብን የመፍጠር ሚናውን ይወጣል።
በሌላ በኩል ማኅበረሰቡ ውስጥ መለውጥ አለባቸው የሚላቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ግንዛቤ በመስጠት ለጋራ ለውጥ ይሠራል፤ የማኅበረሰቡ ለውጥ እንደዜጋ የሱም ለውጥ መሆኑን ስለሚያምን የጋዜጠኝነት መርሆችን ሳያዛባ ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት ይተጋል።
የሀገርን ምሥጢር መጠበቅ፣ እንደ ዜጋ ያወቀውን የመከላከያ ሠራዊትን አቅም ይፋ አለማድረግ፣ በማኅበረሰብ መካከል ግጭት የሚፈጥሩ መረጃዎችን አለማሰራጨት የአንድ ጋዜጠኛ የዜግነት ግዴታው ነው፡፡ ለዚህ ነው ጋዜጠኛ ብሔራዊ ጥቅም አለው የተባለው፡፡
እነዚህ የሀገር ደኅንነትን የተመለከቱ ጉዳዮች እንደ የሀሳብ ነፃነት ካሉ የጋዜጠኝነት መርሆች ጋር በጭራሽ የሚጋጩ እንዳልሆኑ በትላልቅ መገናኛ ብዙኀን ኤዲቶሪያሎች እና በዓለም አቀፍ የጋዜጠኝነት ድንጋጌዎች ላይ ተጠቅሷል፡፡
እንደ ምሳሌ ቢቢሲን ብንወስድ፣ የትኛውም የቢቢሲ ጋዜጠኛ የሀገሪቱን ሚስጢራዊ መረጃዎች አሳልፎ መስጠት እንደማይችል እና እነዚህን ሚስጢሮች መጠበቅ እንዳለበት በሚዲያው ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ተደንግጓል፡፡
በ2025 የተሻሻለው የቢቢሲ ኤዲቶሪያን ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅሞች የሕዝብ ደኅንነት አንኳር ጉዳዮች ስለሆኑ በማንኛውም መልኩ ተላልፈው መሰጠት እንደሌለባቸው እነዚህም ሕዝብን ከሥርዓት ለይቶ መታየት እንዳለባቸው ይደነግጋል።
ጋዜጠኛው ሃይማኖት፣ ወገን፣ ፖለቲካ የለውም ማለት በግሉ እነዚህን የሉትም ማለት ሳይሆን፣ በሥራው ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች እኩል ሽፋን ይሰጣል ማለት ነው፡፡
የጋዜጠኛው የግል እምነት ወይም አመለካከት ምንም ይሁን ምን ከአድልዎ ነፃ መሆንን፣ የግል አመለካከትን ከማንፀባረቅ መጠበቅን እንዲሁም እውነተኛነት እና ትክክለኛነትን መጠበቅን የሞራልም የሕግም ግዴታው ነው።
ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋዜጠኛ የሚቆምለት ዜግነት እና ሀገራዊ ጥቅም እንዳለው በማብራሪያቸው የጠቀሱት፡፡
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #Journalist #nationality