አረንጓዴ አሻራ የተፈጥሮ መልክዓ-ምድርን በመጠበቅ የምግብ ዋስትናን የምናረጋግጥበት አንዱ መንገድ ነው ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የአፋር ክልልን አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በዱብቲ ወረዳ አስጀምረዋል።
በመርሐ-ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የምንተክላቸው ችግኞች የተራቆቱ አካባቢዎች በደን እንዲሸፈኑ በማድረግ የተፈጥሮ መልክዓ-ምድሩን ልንጠብቅበት የምንችልበት ሁነኛ መንገድ ነው ብለዋል።
የሚተከሉ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያላቸው ሚና ላቅ ያለ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም የአርብቶ አደር ማህበረሰቡን ከድህነት በማላቀቅ፣ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጋር በማስተሳሰር በስፋት እንደሚሰራ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ልማት ባለፉት ዓመታት በሰራችው ስራ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት በማግኘት ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ መሆኗን እንዲሁ አንስተዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ህብረተሰቡ፣ የግብርና ባለሙያዎች እና በየ ደረጃው የሚገኙ አመራሮች ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን በመንከባከብ ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ5 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ችግኞች ለመሸፈን እየተሰራ እንደሚገኝ ተነስቷል።
በችግኝ ተከላ መርሐ-ግብሩ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዞን እና ወረዳ አመራሮች እንዲሁም የዱብቲ ወረዳ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።