የሚታይ ለውጥ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን

11 Hrs Ago 68
የሚታይ ለውጥ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን

 

አዲስ አበባ ስሟና ግብሯ  ሆድና ጀርባ ሆነው ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚችው ከተማ  ወዲህ ያማሩና ያሸበረቁ መንደሮች ወዲያ ደግሞ የፈራረሱ ግድግዳዎች፣ በሸራ የተጠጋገኑ ቀዳዳዎች እንዲሁም መሰረታቸው ደግሞ ከፍተኛ ብክለት ባሉባቸው ወንዞችና የነበሩ ቤቶች መገለጫዎች ሆነው ቆይተዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የከተማዋን ነዋሪዎች ሕይወት ለመቀየር ትኩረት ተደርጎ፤ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። 

ታዲያ እነዚህ ሥራዎች ለብዙዎች እፎይታን የሰጡና ከጨለማ ወደ ብርሃን የመውጣት ያክል ስሜትን የፈጠሩ፤ ብሎም የብዙዎችን የሕይወት መንገድ የቀየሩ እየሆኑ ነው።

ታዲያ የከተማ አስተዳደሩ ካከናወናቸው በርካታ ሥራዎች መካከል የኮሪደር ልማት አንዱ ሲሆን፤ በዚህ የኮሪደር ልማት የካዛንችስን  ገፅታ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ቀይሮታል።

በካዛንችስ ብዙ የተጠባበቁና ጣሪያና ግድግዳቸው በላስቲክ የተሸፈኑ፤ ለመኖር ምቹ ያልሆኑ በርካታ ቤቶች ነበሩ።

ወ/ሮ ታደለች ገብሬ ኑሯቸውን በካሳንችስ አነስተኛዋ ደሳሳ ቤት አድርገው ነበር። የቤታቸው መጥበብ እና የንፅህና ጉዳይ በእጅጉ  የሚያሳስባቸው እናት ከሶስት ልጆቻቸው ጋር በዚችው ቤት ተጨናንቀው ይኖሩባት ነበር።

“አንድ ቀን ፈጣሪ ያየን ይሆናል” በሚል በዛው አካባቢ በተለይ በንጽህና ጉድለት ለሚመጡ በሽታዎች ተጋላጭ ሆነው ኖረዋል።

ታዲያ በአንዲት መልካም ቀን ይህንን ሕይወታቸውን ሊቀይር የሚችል ትልቅ የምሥራች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተነገራቸው።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚያች መልካም ቀን ከወ/ሮ ታደለች ቤት በመገኘት ይህ ሁሉ ይቀየራል፤ አይዟቹ ሲሉ ደስታን አበሰሩ።

ወ/ሮ ታደለች አሁን ላይ የዓመታ ፀሎታቸው ሰምሮላቸዋል። ለብዙ ዓመታት በአስጨናቂ ሁኔታ ሲኖሩበት ከነበሩት ቤታቸው ወደ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ገላን ጉራ የነዋሪዎች መንደር አቅንተው የተሻለ ቤት ባለቤት ሆነዋል።

“ከመሬት አንስተው ያማረና ሰፊ ቤት ሰጡኝ” የሚሉት ወ/ሮ ታደለች፤  አሁን ላይ ከሁሉም ሰው እኩል መሆን ችለናል ሲሉ ይናጋራሉ። ቀድሞ የነበራቸው ጉርብትናና ማህበራዊ መስተጋብራቸውም እንዳልተቋረጠ ያነሳሉ።

ሌላኛዋ  በገላን ጉራ የነዋሪዎች መንደር ነዋሪ የሆነችውና እንደ ወ/ሮ ታደለች ዕድል ያገኘችው ወ/ሮ አልማዝ ተሾመ በበኩሏ “ከዚህን ቀደም ስኖርበት የነበረው ኑሮና አሁን ላይ እየኖርኩት ያለሁት በፍጹም አይገናኝም” ትላለች።

በፊት ስኖርበት የነበረው ቤትና ኑሮ ቢወራም አያልቅም የምትለው ወ/ሮ አልማዝ፥  ሰው ቤት እንኳን ለእንግድነት ስሄድ ሶፋ ላይ ለመቀመጥ እሳቀቅ ነበር ስትል ሁኔታውን ታስታውሳለች።

አሁን ላይ ግን  ያማረ ሶፋና አልጋና ሌሎችም ቁሳቁሶች በተሟላ ቤት ውስጥ መኖር ጀምራለች፤ ይህም ትልቅ ደስታና እረፍት  እንደሰጣት ትናገራለች።

“ሁሉም ነገር አሁን አልፏል” የምትለው የዚሁ መልካም ዕድል ተጠቃሚ ሔለን በቀለ ደግሞ፤ በተሻለ መኖሪያ ቤት ከቤተሰቤ ጋር እየኖርኩ ነው ትላላች።

ትላንት በቤቴ መብራት አልነበረኝም የምትለው ሔለን፤ “ዛሬ ላይ ግን  በሳሎን ብቻ ሶስት አምፖሎች አሉኝ፤ ያማረ ቤትም አለኝ” ብላላች። 

ከዚያ ለኑሮ ከማይመች ስፍራ አውጥተው እንደዚህ በሚያምርና ለመኖር ምቹ ወደ ሆነ ስፍራ ያስገቡን አካላት እናመሰግናለን የሚሉት ደግሞ አቶ ኃይሉ ወ/ማርያም ናቸው። 

መንግስት  እኛ በአቅማችን መሥራት የማንችለውን ቤት ሰርቶ ሰጠን፤ እንደ ሙሽራ አዲስ ጎጆ ወጪ ነው የሆነው ሲሉ ይናጋራሉ።

በሐይማኖት ከበደ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top