አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዕከል ከአምስት ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራረመ

3 Yrs Ago
አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዕከል ከአምስት ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራረመ
 
 
አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዕከል ከአምስት ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችሉትን የመግባቢያ ስምምነቶች ዛሬ ተፈራርመዋል፡፡
ከማዕከሉ ጋር ለመስራት ስምምነቶቹን የፈረሙት ዘውዲቱ ሆስፒታል፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ፣ አዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩትና የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ናቸው፡፡
ስምምነቶቹ በፋይናንስ፣ በትምህርትና በጤና ዘርፎች በጋራ ለመስራት እንደሚያስችሉ ተገልጿል፡፡
አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ማሽኖች ሰው ሰራሽ የሆነ የማሰብ ክህሎትን ተጠቅመው የሰው ልጅን ለማገዝ በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ የሚደረግበት ሳይንሳዊ አሰራር ነው።
በጤና፣ በግብርና፣ በትራንስፖርት፣ በሕዝብ ጥበቃና ደህንነት እና በሌሎችም ዘርፎች ጥቅም ላይ በማዋል ለአገር ብልጽግና የሚረዱ የምርምር ውጤቶች ለማፍለቅ እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደገለጹት ማዕከሉ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም፤ ዓላማዎቹን ለማሳካት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የልህቀት ማዕከል ለመሆን መሰረተ ልማትን ጨምሮ በዘርፉ ራሱን የቻለ ፖሊሲ እንዲኖር ዓላማን አንግቦ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ስኬት ከመንግሥትና ከግል ተቋማት ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል።
ስምምነቶቹ የዚሁ አንድ አካል መሆናቸውን ያመለከቱት ኢንጂነር ወርቁ፤ በቀጣይ ሌሎች ተቋማትም ከተቋሙ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ከማዕከሉ ጋር ስምምነቶቹን የተፈራራሙት ተቋማት ኃላፊዎች በበኩላቸው የመግባቢያ ሰነዱ በየዘርፋቸው ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top