በሱዳን የትናንቱ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አራት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

2 Yrs Ago
በሱዳን የትናንቱ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አራት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

በሱዳን የትናንቱ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አራት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

ሰልፈኞቹ የተገደሉት በሱዳን ብሄራዊ ጦር መሆኑ ተገልጿል

በሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተገደሉ ሱዳናዊያን ቁጥር 54 ደርሷል

በሱዳን የትናንቱ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አራት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ፡፡

በጎረቤት ሀገር ሱዳን ከሁለት ወር በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በሚመራው የሲቪል አስተዳድር ላይ መፈንቅለ መንግስት መፈጸሙን ተከትሎ ነበር ሱዳን ወደ ባሰ አለመረጋጋት የገባችው፡፡

በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦርም ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ላይ አርምጃ በመውሰድ ላይ ሲሆን እስካሁን ድረስ 54 ሰላማዊ ሰልፈኞች በሱዳን ጦር በተተኮ ጥይት መገደላቸውን የአገሪቱ ሀኪሞች ማህበር አስታውቋል፡፡

ሰላማዊ ሰልፈኞቹ የሱዳን ጦር ሙሉ ለሙሉ ከስልጣን እስኪወገድ ድረስ ተቃውሟቸውን እንደማያቆሙ በመግለጽ ላይ ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብደላ ሀምዶክ ክህደት እንደፈጸሙባቸውም በመናገር ላይ ናቸው፡፡

የሀገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል አልቡርሃን ሱዳንን ወዳልተፈለገ ብጥብጥ እና ሁከት ስትገባ ጦራቸው ዝም ብሎ እንደማያይ ተናግረው ጦሩ የሱዳንን የዲሞክራሲ አብዮትን በመጠበቅ ላይ መሆኑን አክለዋል፡፡

በትናንትናው ዕለትም የወታደራዊ መንግስት ተቃዋሚዎች አዲስ ህዝባዊ ተቃውሞ ያሰጋቸው የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች የካርቱም ከተማ ጎዳናዎችና መንገዶች ዘግተው ነበር፡፡

የሱዳን ጦር፣ ፖሊሶች እና ፓራሚሊተራዊ ጥበቃዎች በካርቱምን ጎዳናዎች በከፍተኛ ቁጥር ተሰማርተው ፣የመርከብ ኮንቴይነሮች ዋና ከተማዋን ከሰሜን አቅጣጫ ከመንታ ከተማዋ ኦምዱርማን ጋር የሚያገናኘውን የናይል ድልድይ ቢዘጉም ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ግን ወደ አደባባይ ከመውጣት አላቆሙም፡፡

የገለልተኛ ዶክተሮች ኮሚቴ እንደገለጸው፤ የዲሞክራሲ ደጋፊና ማህበረሰብ አንቂዎች በሰራዊቱ ጥቅምት 25 የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት በመቃወም የጎዳና ላይ የሚያደርጉዋቸውን ሰልፎችን እንደቀጠሉ ናቸው።

በሱዳን የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ በህዳር ወር ላይ ከሲቪል ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር አወዛጋቢ ስምምነት ያደረገው መንግስት፤የህዝብን ፍላጎት በመረዳት የህዝብን ቁጣ በማብረድ በኩል ኃላፊነቱ እንዲወጣ ጠይቋል፡፡

ኤምባሲው “በሰላማዊ መንገድ የዲሞክራሲ ፍላጎትን እና የመናገርን ነጻነት የሚለማመዱ ግለሰቦችን ማክበር እና መጠበቅ እንደሚያስፈልግና ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሚያደርግ”ም ገልጿል።

"ኃይልን በመጠቀም ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ እንጠይቃለን እናም ባለስልጣናት በዘፈቀደ ከማሰር እንዲቆጠቡ እናሳስባለን"ም ብሏል ኤምባሲው፡፡ታህሳስ 19 በተካሄደው ተቃውሞ ቢያነስ 13 ሴቶች መደፈራቸው ተመድ መግለጹ የሚታወስ ነው፡

በሱዳን መሪዎች መካከል ያጋጠመውን የፖለቲካ ፍጥጫ ተከትሎ አሁን ላይ በሱዳን የሚሰራ መደበኛ መንግስት አለ ለማለት እንደማይቻል ይገለጻል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top