ኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይን በሰላም እና በንግግር ለመፍታት ከሁሉም ጋር ትሰራለች፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

8 Hrs Ago 99
ኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይን በሰላም እና በንግግር ለመፍታት ከሁሉም ጋር ትሰራለች፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይን በሰላም እና በንግግር እንዲሁም በንግድ ሥርዓት ለመፍታት ከሁሉም ጋር ትሰራለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት የመንግስትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
 
በዚህም የባሕር በር ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የጎረቤት ሀገራትም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አብዛኛው ኢኮኖሚ የተሳሰረ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከተጎዳች እና ሰላም ካጣች ከኢትዮጵያ ባላነሰ ጎሮቤት ሀገራትም ይጎዳሉ ብለዋል።
 
ሀገሪቱ ከአንዳንድ ጎረቤት ሀገራት ጋር የድንበር፣ የንግድ ሥርዓት፣ ሕጋዊ ያልሆነ የውል ችግር እንዲሁም ሌሎች አከራካሪ ያልተፈቱ ጉዳዮች አሉባት ሲሉ ገልጸዋል።
 
በባሕር በር ጉዳይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመከባበር እና በመነጋገር ችግሮችን በመፍታት አብሮ ማደግ ያስፈልጋል፤ ጎረቤት ሀገራትም ይህንን እሳቤ ሊያሰርፁ ይገባል ነው ያሉት።
 
ኢትዮጵያ እያንሰራራች፣ እያደገች እና ልማት እያመጣች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ እንዳይበላሽብን ከጎረቤት ወንድሞቻችን ጋር በሰላም ተከባብረን ለመኖር እንሰራለን ብለዋል፡፡
 
ይሁን እንጂ ተከባብረን መኖር ካልቻልን ራሳችንን እንከላከላለን፤ ለዚያም የሚያሰጋን ነገር የለም፤ ኢትዮጵያ በቂ አቅም አላት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
 
በሔለን ተስፋዬ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top