የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዛሬ በይፋ ስራ መጀመሩን አስመልክቶ ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ መርጋ ዋቅወያ እና የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ደስታ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ፈንዱ በንግድ ባንኮችም ሆነ በአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ለሚቆጥበው ወይም ለሚያስቀምጠው ማህበረሰብ ዋስትና የሚሰጥ ሲሆን፤ በባንኮች ላይ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ የመውደቅ አደጋ ቢያጋጥም አስቀማጮች ካሳ የሚያገኙበት ስርዓት ነው።
በኢትዮጵያ ቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገት የአገሪቱን የፋይናንስ ስርዓት ጤናማ፣ ለአደጋ ያልተጋለጠና የተረጋጋ በማድረግ ለማጠናከር እንዲሁም ለገንዘብ አስቀማጮች ጥበቃ ለማድረግ ሲባል ፈንዱ መቋቋሙ ተብራርቷል።
በተጨማሪም የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድን እንደ አንድ ተጨማሪ የሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ማረጋጊያ ለማድረግ ታስቦ መቋቋሙም በደንቡ ተመላክቷል።
ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በስተቀር ከሕዝብ ተቀማጭ እንዲሰበስቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጣቸው የፋይናንስ ተቋማት በሙሉ የፈንዱ አባል የመሆን ግዴታ ያለባቸው መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መርጋ ዋቅወያ፥ ከዛሬ በኋላ በእያንዳንዱ የፋይናንስ ተቋም ውስጥ ያለው የእያንዳንዱ አስቀማጭ ተቀማጭ ገንዘብ እስከ 100 ሺህ ብር ያለው ገንዘብ በመድን የተሸፈነ መሆኑን ገልጸዋል።
የፋይናንስ ተቋማት ራሳቸው ያስቀመጡት ገንዘብ፣ የፌደራል መንግስት ወይም የመንግስታዊ ድርጅቶች ተቀማጭ ገንዘብ፣ የፋይናንስ ተቋም የውጭ ኦዲተሮች ተቀማጭ ገንዘብ፣ በፋይናንስ ተቋም ተደማጭነት ባለው (ከ2 በመቶ በላይ የአክሲዮን ድርሻ ባለቤት በሆነ) ባለአክሲዮን የተያዘ ተቀማጭ ገንዘብ በመድን ሽፋን ውስጥ አይካተቱም ብለዋል።
የፋይናንስ ተቋማት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የዋና ስራ አስፈጻሚ፣ የከፍተኛ ስራ አስፈጻሚና ከነሱ ጋር የመጀመሪያ የስጋ ዝምድና ያላቸው ግለሰቦች ተቀማጭ ገንዘብም በመድን ሽፋን አይካተቱም።
ወደፊት ፈቃድ የሚወስዱ ባንኮችና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ተቀማጭ መሰብሰብ ከመጀመራቸው በፊት የፈንዱ አባል መሆን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የፈንዱ አባል የሆኑት የፋይናንስ ተቋማት በየዓመቱ ከያዙት ወይም ካላቸው አማካይ ተቀማጭ ገንዘብ 0 ነጥብ 3 በመቶ ለፈንዱ መክፈል እንዳለባቸውም ነው አቶ መርጋ ያስረዱት።
በመድን ፈንዱ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መሰበብሰቡና በበጀት ዓመቱ 6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን አብራርተዋል።
ከፋይናንስ ተቋማት ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድ እንደተገዛበትና ቀሪው 100 ሚሊዮን ብር የሸሪዓ መርህን በተከተለ መልኩ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሙዳረባህ ኢንቬስትመንት ሂሳብ እንዲቀመጥ መደረጉን ጠቅሰዋል።
መንግስትም መነሻ ካፒታል እንዲሆን ለፈንዱ 200 ሚሊዮን ብር እንደሚመድብ ደንቡ በደነገገው መሰረት የገንዘብ ሚኒስቴር የፈንዱን ስራ ለመጀመር 25 ሚሊዮን ብር መልቀቁን ጠቁመዋል።
መንግስት ፈንዱ ስራውን እንዲጀምር ቢሮ ማደራጀትና ሎጅስቲክስን ጨምሮ ወሳኝ ድጋፍ ማድረጉንና የዓለም ባንክም ለፈንዱ የአቅም ግንባታ ስራዎች ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ደስታ፤ ባንኮች ላይ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ የመውደቅ አደጋ ቢያጋጥም ገንዘቡ ለአስቀማጮች የሚመለስበት አሰራር መዘጋጀቱን አመልክተዋል።
በተጨማሪም የፈንዱን ገንዘብ ላልተፈለገ ዓላማ የሚጠቀሙ አካላትም በፈንዱ ማቋቋሚያ ደንብ መሰረት በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል።
በአጠቃላይ የፈንዱ መጀመር ትልቅ ስኬት እንደሆነና ከለውጡ በኋላ በፋይናንስ ዘርፉ የተካሄዱ ሪፎርሞች ውጤት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ያቋቋመች 148ኛ አገር መሆኗ በመግለጫው ወቅት ተጠቅሷል።