የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤትን ለተቀላቀሉ አባል አገራት አቀባበል ተደረገ

1 Mon Ago 505
የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤትን ለተቀላቀሉ አባል አገራት አቀባበል ተደረገ

አቀባበል የተደረገላቸው ሀገራት አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ኮትዴቯር፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብጽ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋምቢያ፣ ሴራሊዮን፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ናቸው።

በአቀባበል መርሃ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዴዬ፤ ባለፋት 20 ዓመታት ምክር ቤቱ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራትና የመጡ ለውጦችን ተናግረዋል።

የጥይት ድምፅ የማይሰማባትን አፍሪካ እውን ለማድረግ ሰፊ ጥረት ስለመደረጉ አስታውሰው፤ የተቋማት ግንባታ ላይም አዳዲስ አሠራሮች ተዘርግተው ተግባራዊ ተደርገዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነትና ሌሎች የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካ በመፍታት ጥይት የማይሰማባትን አፍሪካ እውን ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራትን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት በቀጣቶቹ አሥር ዓመታትም በአህጉሩ ግጭቶችን መከላከል ላይ ዋነኛ ትኩረቱ አድርጎ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአባል አገራት የሚስተዋሉ ግጭቶች አሁንም መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በተለይም በሱዳን የቀጠለው ግጭት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

በአፍሪካ ሽብርተኝነትን መታገል፣ ሀገራት ለሰላምና ጸጥታ በትብብር እንዲሰሩ ማገዝ፣ የዴሞክራሲ ባህልን ማሳደግና ሌሎች ጉዳዮችም ቀጣይ ትኩረት ይሰጣቸዋል ሲሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

እ.ኤ.አ. በ2030 የጥይት ድምፅ የማይሰማባት አፍሪካን እውን ለማድረግ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በትብብር እንስራ በማለትም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤትን የተቀላቀሉ አባል አገራት ለዚህ ግብ  መሳካት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት 15 አባል አገራት ያሉት መሆኑ ይታወቃል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top