ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር ምን አገኘች?

5 Mons Ago 1141
ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር ምን አገኘች?
በኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የኢትዮጵያን የደን ሽፋን አሳድጎታል።
 
ታዲያ በ2019 በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ማለት ነው 17.2 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ዛሬ ላይ 23.6 በመቶ ደርሷል።
 
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የደን ሽፋኑን ከማሳደግ በዘለለ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ዕድገት ላይ ምን አስተዋፅኦ አበርክቷል? ስንል በኢትዮጵያ ግብርና ኢንስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚ ተመራማሪን ዶ/ር አበባው አሳዬን አናግረናል።
 
"የአረንጓዴ አሻራ በግብርና ስራችን ላይ ዘርፈብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። ነገር ግን ለውጡ እና ጥቅሙ በአንዴ የሚታይ አይደለም" ያሉት ተመራማሪው ዘላቂ ግብርናን ለማገዝ ምርታማነትን ለማሳደግና ለማሻሻል የረጅም ጊዜ አስተዋጾው ቀላል አለመሆኑን ገልፀዋል።
 
ለዚህም ማሳያ አድርገው ዶ/ር አበባው ያነሱት "የደን ልማት ስራ ይሰራበታል፣ የተጎዳ መሬት እንዲያገግም ይረዳል፣ የአፈር ለምነት እንዲሻሻል፣ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ መሬት የውኃ መያዝ መጠኑ ከፍ እንዲል፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ግብርናችን የተሻለ እንዲሆን እና ሰብሎች የአየር ንብረት ለውጡን እንዲቋቋሙ በማድረግ ምርታማነትን እንዲጨምር ያረጋል" ብለዋል።
 
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሩ ድርቅን በመከላከል ዘላቂ የውኃ ፍሰትን የመያዝ አቅምን በመጨመር ዘላቂ ግብርና እንዲኖረንም የሚያስችል ስለመሆኑ ተናግረዋል።
 
በተጨማሪም የሚተከሉ ችግኞች ለምግብነትም የሚውሉ በመሆናቸው የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ ያግዛሉ ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም አቀፉ ትኩረት አቅጣጫ ነው ያሉት ዶ/ር አበባው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በአየር ብክለት ቅነሳው አስተዋፆ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
 
ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት 40 ከመቶ በላይ የደን ሽፋን እንደነበራት የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ።
 
 
ነገር ግን በነበረው ዘላቂ ያልሆነ የመሬት አጠቃቀምና የተፈጥሮ ሁኔታ የደን ሽፋኑ ወደ 3 በመቶ ዝቅ ብሏል።
 
ይሄው የመሬት መሸርሸር እና የተፈጥሮ ሐብት መራቆት ደግሞ ሕዝቡን ለድህነትና ለረሀብ ሲያጋልጥ ቆይቷል።
 
በ2011 ዓ.ም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የተጀመረው።
 
በናርዶስ አዳነ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top