በጎፋ ዞን ከደረሰው የመሬት መንሸራተት የተረፉት ኢንስፔክተር ምን ያስታውሳሉ?

1 Mon Ago 678
በጎፋ ዞን ከደረሰው የመሬት መንሸራተት የተረፉት ኢንስፔክተር ምን ያስታውሳሉ?

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ቀበሌ ከተከሰተው መሬት መንሸራተት በተዓምር ተርፈው ለዛሬው ምስክርነት የበቁት ኢንስፔክተር በዛብህ ቡናሮ አደጋው ሲከሰት መረጃው እንደደረሳቸው ባለድርሻ አካላትን ይዘው የነፍስ አድን ስራ ለመስራት ይወስናሉ፡፡

ከወረዳው ማዕከል 10 አባላትን ይዘው ወደ ስፍራው ያቀኑት የገዜ ጎፋ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር በዛብህ፤ የቀበሌው አስተዳዳሪ ከነሙሉ ቤተሰባቸው ናዳው ስለተጫናቸው እነሱን ለማዳን የአካባቢው ነዋሪዎች ሲረባረቡ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ታዲያ በዚህን ሰዓት ያልተጠበቀ ፍንዳታ ከኋላቸው በቅርብ ርቀት መፈጠሩን ተከትሎ ሌላ አደጋ መፈጠሩን እና ለነፍስ አድን የተሰበሰቡ ከ200 የሚልቁ የአካባቢው ነዋሪዎች በቅጽበት በናዳው ከመሬት ስር ሆኑ ይላሉ በተሰበረ ልብ፡፡

አብረዋቸው ከነበሩ ባልደረቦች መካከል ሁለቱ ወዲያውኑ የተከሰተው ናዳ ሲወርድ ይዟቸው እንደወረደ የሚናገሩተ ኢንስፔክተር በዛብህ፤ ከቀሪ የስራ ባለደረቦቻቸው እና የወረዳው አስተዳደሪን ጋር በመሆን ከአደጋው ሮጠው “በተዓምር” ማምለጣቸውን ነው የገለፁት፡፡

ከዚህ በኋላ ለዞን፣ ለክልል አደጋ ስጋትና ስራ አመራር መዋቅሮች የድረሱልኝ ጥሪ ማሰማታቸውን በተለይም ለኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ተናግረዋል፡፡

አደጋውን ይበልጥ የከፋ ያደረገው የወረዳው አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ባለሙያዎች ከመድረሳቸው በፊት ነዋሪዎች የነፍስ አድን ስራ ለመስራት የአደጋ ክልል ውስጥ በመግባታቸው እንደሆነም ገልጸዋል ኢንስፔክተር በዛብህ ቡናሮ።

አደጋው የከፋና ቅጽበታዊ በመሆኑ ከአካባቢው መራቅ እንዳለባቸው የማያውቁትን ይቅርና የሚያውቁት እራሱ ራሳቸውን ማዳን ያልቻሉበት ሁኔታ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የገዜ ጎፋ ወረዳ አካል የሆነውና የመሬት ናዳ አደጋ ስጋት አለበት የሚባለው አካባቢ ስፋት በግምት ወደ 150 ሄክታር ስፋት እንዳለው የሚናገሩት ኢንስፔክተሩ፤ የመሬት አቀማመጡ በተፈጥሮ ተራራማ፣ ገደላማና ወጣ ገባ የሚበዛበት መሆኑን ጠቁመዋል።

እንዲህም በመሆኑ አደጋው ሲከሰት ቶሎ ሰዎችን ለማዳን ርብርብ ከመደረጉ ውጭ ሊናድ ይችላል ተብሎ በአይን ሊታወቅ የሚችል ምንም ምልክት ለማየት የማይቻልበት እንደነበር ገልጸዋል።

አካባቢው ባቄላ፣ አተር፣ ስንዴና ገብስ እንዲሁም እንሰት በብዛት የሚመረትበት ለም መሬት ያለው በመሆኑም ነዋሪዎች ለቀው መውጣት አይፈልጉም የሚሉት ኢንስፔክተር በዛብህ፤ አደጋው ከደረሰ ጀምሮ እየተደረገ ያለው ርብርብ የአደጋው ሰለባዎች እስኪያገግሙ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

በመሀመድ ፊጣሞ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top