ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም ባካሄደው የተማሪዎች ምረቃ ለጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ይታወሳል።
በእለቱ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በስራ መደራረብ ምክንያት በምረቃ እለቱ ተገኝተው ባለመቀበላቸው ዛሬ ህዳር 16/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ስካይላይት ሆቴል በአካል ተገኝተው ተቀብለዋል።
የክብር ዶክተር መአዛ ብሩን ለክብር ዶክትሬት ሽልማት ያበቋቸው ስራዎች በዝርዝር:-
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ2015 ዓ.ም የተማሪዎች ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የመጀመሪያዋ የክብር ዶክትሬት ተሸላሚ የጠንካራ ጋዜጠኝነት ተምሳሌቷ እና የባለታሪኮች ባለአደራ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ናት።
ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ:-
- በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ የሸገር መስራች እና ባለቤት፤
- የመጀመሪያዋ ሴት የሬዲዮ ማሰራጫ ድርጅት መስራችና ባለቤት፤
- በእንግዶች ምርጫዋ፤ በምርምር በተደገፈ የመጠይቅ ዘይቤዋ፣ በትህትናዋ፣ በአነጋገር ለዛዋ በቀጥታ አዘጋጅታ ከምታቀርባቸው ፕሮግራሞች (የቅዳሜ ጨዋታ እና ሸገር ካፌ) በተጨማሪ በተለያዩ የሸገር ሬዲዮ ፕሮግራሞች እንዲሁም በሌሎች ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ አሻራ የተወች እና ባጠቃላይ በዚህ ዘርፍ ለተሰማሩ ጋዜጠኞች አርአያ የሆነች፤ ምናልባት ከሁሉ በላይ ታዋቂ የሆነችበትና አምሳያ የሌለው የላቀ አስተዋፅኦ ተብሎ ሊወሰድ ከሚችሉት ስራዎቿ ውስጥ አንዱ፤ በቀላሉ ተተኪ የማይገኝላቸውን በርካታ ባለታሪክ ምሁራን፣ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች፤ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፤ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች የህይውት ታሪክ፤ ስራ፣ አስተሳሰብ እና ለሌሎች አርአያ የሚሆነውን የሕይዎት ፍልስፍናቸው በራሳቸው አንደበት ተሰናድቶ ለታሪክ እንዲቆይ ማድረጓ ነው። በዚህም ለኢትዮጵያውያን በዓይነቱ ተወዳዳሪ የሌለውና ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የሚሄድ የታሪክ የድምጽ መዘክር አበርክታለች ማለት ይቻላል።
የጨዋታ እንግዳ መሰናዶ እንግዶቿ ያካበቱት ልምድ፤ አበርክቶአቸው፤ ያልተጻፉ ሃገራዊ ጉዳዮች እና ሚስጥሮች ከኃላፊ ባለታሪኮቹ ጋር እንዳያልፉ፤ በመቅረጸ ድምጽ ተሰንቀው በሰፊው እንዲታወቁ እና ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ አድርጋለች። በእርግጥም ጋዜጠኛ መዓዛ ከየተደበቁበት ፈልጋ ቃለ መጠይቅ ካደረገቻቸው ጉምቱ እንግዶች መካከል ጥቂት የማይባሉት አሁን በመሃከላችን አይገኙም፤ ታሪካቸው ግን ህያው ሆኗል።
ጋዜጠኛ መዓዛ በ1950ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ የተወለደች ሲሆን ዘጠኝ ዓመት ገደማ እስኪሆናት በምዕራብ ሃረርጌ በምትገኘው ሂርና ከተማ አደገች። ሂርና ሳለች ጎረቤቶቿ የኦሮሞ፣ የሃረሪና የሶማሌ የየመን ተወላጆች ስለነበሩ በተለያዩ ባህላዊ ዕሴቶች እና እርስ በእርስ ትስስር የዳበረ አስተዳደግ ነበራት። ይህም፣ ለስነ-ጽሁፍ ከነበራት ዝንባሌ ጋር ተዳምሮ ለዛሬው ማንነቷ መሰረት ሆኗታል።
- ጋዜጠኛ መዓዛ ዘጠኝ ዓመት ሲሆናት ወላጆቿ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የቅድስተ ማርያም የልጃገረዶች ካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት አሰገቧት።
- በ1967 ዓ.ም የሁለትኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለች በእድገት በህብረት ዘመቻ ወደ ውቅሮ ትግራይ ተልካ ለስድስት ወራት አገልግላለች።
- በ1970 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብታ በስነ ልሳን ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች።
- ከሬዲዮ ስራ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀችው የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለች በአጋጣሚ ሲሆን በወቅቱ ተወዳጅ ከነበረው የእሁድ ፕሮግራም ጋር ለነበራት ለስምንት ዓመታት ያክል የቆየ ትሥሥር ምክንያት ሆኗታል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ በቋሚነት የተመደበችበት ስራዋ በባህል ሚኒስቴር ስር የመርሃ ስፖርት ጋዜጣ የስፖርት ዘጋቢነት ነበር።
- በመቀጠልም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ ፕሮግራም ተሳትፎዋን ሳታቆም በባህል ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ አገልግሎት ክፍል አገልግላለች።
- ከዚያም በብሄራዊ ባንክ የብሪቱ መጽሄት ዋና አዘጋጅ በመሆን የፋይናንስ ዜናዎችን እና አጫጭር ታሪኮችን በመጻፍ እና በአርትኦት አገልግላለች።
- በ1984 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ተቀላቅላ የፕሬስ እና ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር በመሆን ለአራት ዓመታት ሰርታለች።
- ከዚያም በግል በአማካሪነት እና በህዝብ ግንኙነት እና ማስታወቂያ ስትሰራ ከቆየች በኋላ በ1987 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የኤፍኤም 97.1 ሬዲዮ ጣቢያን የአየር ሰዓት በመጠቀም የቅዳሜ ከሰዓት የጨዋታ ፕሮግራምን ከባለቤቷ ከአርቲስት አበበ ባልቻ እና ከረዥም ጊዜ ጓደኛዋ አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ ጋር የማዘጋጀት ዕድል አግኝታ ፕሮግራሙን ለስምንት ዓመታት ያክል ስታቀርብ ቆይታለች።
- በመጨረሻም በ2000 ዓ.ም አንጋፋና ተወዳጅ የሆነውን ሽገር ኤፍ ኤም 102.1ን እዉን ለማድረግ በቅታለች።
በአጠቃላይ:
ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ የጥንካሬ ተምሳሌትና በዘርፉ ለበርካቶች አርአያ ለመሆኗ ተገቢ እውቅና ይሆን ዘንድ የባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ ሴኔት በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152/2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት በአርት የዓመቱ የክብር ዶክትሬት እንዲሰጣቸው መወሰኑን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።