የነዳጅ ድጎማን በህገወጥ መንገድ ሲጠቀሙ የነበሩ 40 ሺህ ተሽከርካሪዎች ከስርዓቱ እንዲወጡ ተደርጓል - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

3 Mons Ago
የነዳጅ ድጎማን በህገወጥ መንገድ ሲጠቀሙ የነበሩ 40 ሺህ ተሽከርካሪዎች ከስርዓቱ እንዲወጡ ተደርጓል - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

የታለመለት የነዳጅ ድጎማን ላልተገባ ዓላማ ሲጠቀሙ የነበሩ 40 ሺህ ተሽከርካሪዎች ከድጎማ ስርዓቱ እንዲወጡ እና ዕዳ እንዲከፍሉ መደረጉን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ይህን ያሉት የመንግሥት የ2016 የመጀመሪያ የሩብ ዓመት አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት ነው።

የግምገማው ተሳታፊዎች መንግሥት የነዳጅ ድጎማን ጨምሮ በርካታ የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጡ ተግባራትን ማከናወኑን አድንቀው፤ ሆኖም" ድጎማው ሃብታሞችን እንጂ ድሃውን ማህበረሰብ በሚፈለገው ልክ አልጠቀመም" ሲሉ ተችተዋል።

መንግሥት የችግሩን ጥልቀት ምን ያህል ያውቀዋል፤ ምንስ እርምጃ ወስዷል ሲሉም ጠይቀዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም በሰጡት ምላሽ፤ መንግስት የድጎማ ስርዓቱን ሲዘረጋ አቅም የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በብዙሃን ትራንስፖርት ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ስርዓቱ መተግበር ከጀመረ ወዲህ 23 ቢሊዮን ብር በብዙሃን ትራንስፖርት ለተሰማሩ አካላት በድጎማው አማካይነት መሰጠቱን አስረድተዋል።

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት  ሌላኛው ዓላማ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ታሪፍ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ሆኖም አፈጻጸሙ ላይ ችግር መስተዋሉን ገልጸዋል።

ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የተሰጣቸውን የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉና በህገወጥ መንገድ ሲጠቀሙ የነበሩ ተሽከርካሪዎች መኖራቸው በክትትል እንደተደረሰበት ተናግረዋል።

በዚህም በጥቆማና በትክክለኛ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ በተወሰደው እርምጃ፤ ድጎማውን ላለተፈለገ ዓላማ ሲጠቀሙ የነበሩ 40 ሺህ ተሽከርካሪዎች ከድጎማ ስረአቱ እንዲወጡ መደረጉን ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ መንግስት ለህዝብ ተጠቃሚነት እንዲሰሩ ሲሰጣቸው የነበረውን የድጎማ ገንዘብ በዕዳ መልኩ መልሰው እንዲከፍሉ መደረጉን አስረድተዋል።

ዶክተር ፍጹም አክለውም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ነዳጅን በህገወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩና በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ የሚልኩ አካላት ላይ በጥብቅ ክትትል እርምጃ ተወስዷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ነዳጅ ከመነሻ ወደብ እስከ ተጠቃሚው የሚደርስበት አጠቃላይ ሰንሰለት ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቁጥጥር ለማድረግ የዲጂታል ስርዓት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top