በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሥርጭት በስፋት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የቅድመ መከላከል ስራ በትኩረት ይሰራል፡-የጤና ሚኒስቴር

7 Mons Ago
በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሥርጭት በስፋት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የቅድመ መከላከል ስራ በትኩረት ይሰራል፡-የጤና ሚኒስቴር

በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሥርጭት በስፋት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የቅድመ መከላከል ስራው በትኩረት እንደሚሰራ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የዓለም ኤድስ ቀን "የማህበረሰብ መሪነት የኤች አይ ቪ ቫይረስ መከላከል" በሚል መሪ ሀሳብ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ36ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የዓለም ኤድስ ቀን ሲከበር ህብረተሰቡ የኤች አይ ቪ ቫይረስ በመከላከል የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ሚኒስቴሩ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡

የኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭት ምጣኔን በመከላከል ረገድ መንግስትና ማህበረሰቡ ባደረጉት ጥረት እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር  በ2010 ከነበረበት 1 ነጥብ 26 በመቶ  በ2022  ወደ 0 ነጥብ 91 በመቶ መቀነስ  መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል ተብሎ ከሚገመቱ ሰዎች መካከል 84 በመቶ የሚሆኑት ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁና ከነዚህም ውስጥ 98 በመቶው የጸረ-የኤች አይ ቪ መድሃኒት እንዲጠቀሙ ማድረግ ተችሏል።

ነገር ግን አሁንም የቫይረሱ ስርጭት በስፋት የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች በመኖራቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ስርጭቱን ለመግታት እንደሚሰራ ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

በተለይ የመገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም አጀንዳ በማድረግ በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸው፤ ችግሩን ለማጥፋት ግን  አፍላ ሴት ወጣቶች ላይ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የኤች አይቪ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ፍቃዱ ያዴታ በበኩላቸው፤ የዓለም አገራት በ2030 ኤች አይ ቪ ኤድስ ለማኅበረሰቡ ሥጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ጥረት በማረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተ.መ.ድ የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል መርሃ ግብር (ዩ ኤን ኤድስ) ዳይሬክተር ፍራኮዝ ናዪሺሚ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባለፉት ዓመታት አመርቂ ስራዎች እንደተሰሩ ገልጸዋል።

በተለይ  የማህበረሰብ  አቀፍ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ስራው የቫይረሱ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በመድረኩ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ በዘርፉ የሚሰሩ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ አምባሳደሮች፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top