በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የተቀረጸ ብሔራዊ ስትራቴጂ ዕቅድ እና የድርጊት መርሀ ግብር ይፋ ሆኗል።
ስትራቴጂ ዕቅድ እና የድርጊት መርሀ ግብሩ ሴቶች እና ህጻናት ያለምንም የጥቃት ስጋት መብታቸውን ማጣጣም እንዲችሉ እንዲሁም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ህጻናት የተጠናከረ የመረጃ እና የድጋፍ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
በተጨማሪም በፍትህ ሥርዓት ውስጥ ለሚያልፉ ህጻናት ሊደረጉ የሚገባቸው የጥበቃ እና እንክብካቤ ሥራዎችም በሰነዱ መካተቱ ተጠቁሟል፡፡
ቀደም ብሎ ተዘጋጅቶ የነበረው ስትራቴጂ የትግበራ ዘመኑ የተጠናቀቀ በመሆኑ፤ ዓለም አቀፍ ሰነዶችና ተሞክሮዎች ባገናዘበ መልኩ ለቀጣዮቹ አምስት አመታት እንዲያገለግል ታስቦ መዘጋጀቱም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
የ16ቱ ቀናት የጸረ ጾታዊ ጥቃት ቀን የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሀ ግብርን ምክንያት በማድረግ በተቀናጀ መልኩ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል፣ ምላሽ ለመስጠት እና የህጻናት ፍትህን ለማረጋገጥ ያለመ ብሔራዊ ሎጎ በይፋ ተመርቋል።
በሌላ በኩል፤ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ህጻናትን ለመደገፍ እንዲሁም ለጥቃት የተጋለጡ ሴቶች እንዲያገግሙ እና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማስቻል በአዳማ ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጎብኝተዋል።