በሱስ የተያዙ ሰዎች በአዕምሮ ህመም የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን የስነ ልቦና ባለሙያው ዳዊት ላቀው ተናግረዋል፡፡
ሱስ ከአዕምሮ ህመም ጋር ከፍተኛ ግንኙነት እናዳለው እና ሰዎች በሱስ ውስጥ ሲገቡ ወይንም ደግሞ ሲጠመዱ ትክክለኛ የሆነ አዕምሮአቸውን እንዳይጠቀሙ ያደርጋቸዋል ሲሉ ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡
ከኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት ባለሙያው፤ ሱስ አስተሳሳብን የመያዝ እና የሰዎችን ባህሪ የመቀየር አቅም ስላለው፤ ጠንካራ ስነ ልቦና የነበረው ሰው በሱሱ ምክንያት ጭንቀት ውስጥ በመግባት ለአዕምሮ ህመም እንደሚያጋልጥ ገልጸዋል፡፡
ሱስ ያለባቸው ሰዎች በስነልቦናው በብዙ መንገድ ይታያሉ የሚሉት ባለሙያው፤ በእለት ከእለት ሕይወታቸው ውስጥ በሱስ የተያዙበትን ነገር ካላገኙ መደበኛ ስራቸውን መስራት እና ትክክለኛ ባህሪያቸውን ማሳየት እንደማይችሉ ነው የሚናገሩት፡፡
ሰዎች በአቻ ግፊት እና በሕወት ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች ወደ ተለያዩ ሱሶች እንደሚገቡ የስነልቦና ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡
ሱስ ሰዎች ችሎታቸውን እና አቅማቸው እንዳያወጡ ከማድረግ አልፎ፣ የበታችንት ስሜት እንዲሰማቸው እና ለራሳቸው የሚሰጡትም ግምት ዝቅ እንዲል እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡
በሱስ መጠመዳቸው በማህበራዊ መስተጋብራቸው የእለት ከእለት ሕይወታቸው ላይ ጫና እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
በሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎች የቁጭት ስሜት እንደሚሰማቸው የሚያነሱት ባለሙያው፤ ይሄም ነገሮችን በራሳቸው ማድረግ ስለሚያቅታቸው እና አቅማቸውን እንዲያወጡ ስለማያስችላቸው፤ በሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎች ጸጸት ውስጥ የመግባት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ይላሉ፡፡
ሱሰኝነትን በአንድ ጊዜ ወይም በቅጽበት ለመተው ከማሰብ ይልቅ፤ መጠንን እየቀነሱ ለዘለቄታው እስከመተው መድረስን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ብዙዎች ይመክራሉ፡፡
የስነልቦና ባለሞያ ጋር በመቅርብ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ስለመሆኑም ባለሙያው ይመክራሉ፡፡