ፀቤ ከንጉሡ እንጂ መች ከሀገሬ ነው የሚሉት ጀግና፡- ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (ባልቻ አባ ነፍሶ)

7 Mons Ago 1321
ፀቤ ከንጉሡ እንጂ መች ከሀገሬ ነው የሚሉት ጀግና፡- ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (ባልቻ አባ ነፍሶ)

ሀገር እና መንግሥት ለይተው የተረዱ የሀገር ባለውለታ ናቸው፡፡ ታማኝነታቸው ለሀገራቸው ብቻ መሆኑን በተግባር ተፈትነው ያስመሰከሩ ወደር የለሽ ጀግና ናቸው፡፡ ወደር ለሌላቸው ጀግንነታቸው በትውልድ ሲወሱ ይኖራሉ፡፡

“እንደ ደጋ ገብስ እንዲያ ኮስሶ

ያስቆረጥማል ጠላቱን ኮሶ

የዳኘው ጀግና ባልቻ አባ ነፍሶ”

የተባለላቸው የአድዋው ጀግና! ጣሊየንን ሁለት ጊዜ በመዋጋት ባለታሪክ የሆኑት የነጻነታችን አርማ ደጃዝማች ባልቻ ሰፎ (ባልቻ አባ ነፍሶ)!

በቤተ መንግሥት ውስጥ በጦር ሙያ ተኮትኩተው በጎልማሳነታቸው የመድፍ ተኩስ ተምረዋል፡፡ ከአድዋ ጦርነት በፊትም የቤተ-መንግሥቱ ግምጃ ቤት ሹም ሆነው በታማኝነት አገልግሎታቸውን አበርክተዋል፡፡

ደጃዝማች ባልቻ በ33 ዓመታቸው 3 ሺህ ጦራቸውን መርተው ዓድዋ ላይ አኩሪ ታሪክ ሰርተዋል፡፡ የአምባላጌን ምሽግ በጀግንነት የሰበሩት ፊታውራሪ ገበየሁ የካቲት 23 ብዙ ሰው ተጎድቶበት እያፈገፈገ የነበረውን ጦራቸውን ለማጀገን ራሳቸው በግንባር ወደ ጦርነቱ ገብተው ከተሰው በኋላ ደጃዝማች ባልቻ የመድፍ ተኳሽነቱን ድርሻ ያዙ፡፡ በዚህም፡-

"ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፤

መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፡፡"

ተብሎ ተገጠመላቸው፡፡

በዓድዋው ጦርነት ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ከሊቀ-መኳስ አባተ ጋር በመሆን በመድፍ ስላደረጉት ፍልሚያ በርክሌይ ሲጽፍ፣ “ጣሊያኖች እንዳሥላሴ ወጥተው ‘የኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንን ልቀቁ፤ ጦርነቱ ሲያልቅ በትልቅ ህንጻ እንሰራላችኋለን።’ አሏቸው እና አንድ ሺህ ብር ሰጧቸው። ሁሉም ቤተክርስቲያኑን ሲለቁ አንድ የሃምሳ ዓመት ቄስ ግን እምቢ አሉና ወዲያውኑ ተገደሉ። ከዚያም ቤተ ክርስቲያኑንና ቦታውን ጣልያኖች ተቆጣጠሩት። ሆኖም ክርስቲያን የሆኑ የጣሊያን ወታደሮች ‘ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተን አንዋጋም’ በማለታቸው ክርስቲያን ያልሆኑ ወታደሮች እዚያ ገብተው ጦርነቱ ቀጠለ፤ ያ ቀን መጥፎ እለት ነበር።

በጣሊያኖቹ ወገን ከእንዳሥስላሴ የሚተኮሰው መድፍ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ጨረሰ። በኢትዮጵያ በኩል የተተኮሰው የመድፍ ጥይት፤ የጣሊያኑ መድፍ አፍ ውስጥ ገብቶ ሁለት ወታደሮችን አቆሰለ… እሳትም ተነስቶ አፈር የተሞሉ የምሽግ ጆንያዎች ተቃጠሉ።” ብሏል።

የደጃዝማች ባልቻ የጀግንነት ታሪክ በተለይ ከዓድዋ ድል በኋላ እየገነነ መጥቶ በአጼ ምኒልክ ዘመን የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ሲቋቋም፣ የግምጃ ቤቱ ኃላፊ ሆነው የኢትዮጵያን ጦር መሳሪያ በዓይነት በዓይነት ማስቀመጥ መጀመራቸው ይነገራል። የጦር ግምጃ ቤቱ ከአጼ ምኒልክ ጀምሮ እስከ ደርግ ዘመን ድረስ የነበሩ መድፍ እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን እንደያዘ ግንቦት 27 ቀን 1983 ዓ.ም "በበቅሎ ቤት ፍንዳታ" ተቃጥሏል፡፡

በዕድሜ እና በእውቀት እየበሰሉ ሲመጡም የሲዳሞ ሀገረ ገዢ ሆነው ተሾሙ። በኋላም የራስ መኮንን የመጀመሪያ ልጅ ደጃች ይልማ ሲሞቱ የሐረርጌ ገዢ እንዲሆኑ በልጅ እያሱ አማካኝነት ተሾሙ። ራስ ተፈሪም የወላይታ ገዢ ሆነው በልጅ እያሱ አማካኝነት ተሾመ።

ደጃች ባልቻ አባ ነፍሶ ሐረርጌን ለአራት አመታት ካስተዳደሩ በኋላ ራስ ተፈሪ፣ “የአባቴ ሀገር ሐረርጌን ላስተዳድር?” በሚል ጥያቄ ወደ ተሾሙበት ግዛት ሳይሄዱ አዲስ አበባ ላይ ከረሙ። ይህም ደጃዝማች ባልቻ እና ራስ ተፈሪ መካከል ቅሬታን ፈጠረ፡፡

ራስ ተፈሪ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተብለው የንጉሠ ነገሥትነቱን ዙፋን ሲይዙ፣ ባልቻ አባ ነፍሶን ከቀድሞ የአገር አስተዳዳሪነት ሹመት አነሷቸውና ደጃዝማች ብሩ ወልደገብርኤልን ሾሟቸው። ይህም ሆኖ ግን ባልቻ አባ ነፍሶ በወቅቱ በነበሩት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ጭምር እንደተከበሩ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ሄደው ተቀመጡ።

ከዚህ በኋላ ደጃዝማች ባልቻ ከነ ሙሉ ክብራቸው፤ በአካባቢው ህዝብ እንደተወደዱ፤ ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ጋር ወደ ሌላ ጸብ ሳይገቡ፤ ከነልዩነታቸው በሰላም ተለያይተው መኖር ጀመሩ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ሀገር እያስተዳደሩ፤ ደጃች ባልቻም የተጣላ እያስታረቁ፤ እስከ ሁለተኛው የጣልያን ወረራ 1928 ዓ.ም. ድረስ ዘለቁ።

የዓድዋው ጦርነት ሥመ ጥር ጀግና ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ፋሽስት ጣልያን ኢትዮጵያ በድጋሚ ስትወር ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋራ ፀብ ስለነበራቸው ባልቻ ከጣልያን ጎን ይሰለፋሉ ብለው ጣልያኖች አሰቡ። ደጃዝማች ባልቻ በንጉሱ ላይ ቅሬታ ቢኖራቸውም በሀገር ጉዳይ ላይ ሌላ ድርድር መግባት አልፈለጉም፤ ስለሆነም ጦራቸውን ማሰባሰብ ጀመሩ እናም ከነ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ፣ አበበ አረጋይ፣ በላይ ዘለቀ እና አቡነ ጴጥሮስ ጋራ ስለ ጦርነቱ የሚስጥር ደብዳቤ መለዋወጥ ጀመሩ።

ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ አምስት ሺህ ጦራቸውን ይዘው በ74 ዓመታቸው ከትውልድ መንደራቸው ተነስተው አዲስ አበባ ደረሱ ከዛም ረጲ ተራራ ላይ ሆነው መድፋቸውን ጠምደው የሌሎችን አርበኞች መልዕክት ይጠባበቁ ጀመር። የባልቻ ሰላይ የነበሩት ሰው በባንዳ ተይዘው ሲገደሉ ጣሊያን በአውሮፕላን ሆኖ የደጃዝማች ባልቻ ጦርን እየተከተለ በጣም ብዙ ሰው ጎዳባቸው።

ብዙ ወታደሮቻቸው የሞቱባቸው ጀግና ብቻቸውን ቀሩ። ፊታውራሪ ገብረ መድህን እና ፊታውራሪ ሳህለሚካኤል የተባሉ ሁለት ወንድሞቻቸውም በጣሊያን ጦር ተማርከው ተገደሉ።  ደጃዝማች ወንድሞቻቸውን በማጣታቸው የደረሰባቸውን ሀዘን እንዲህ በማለት ገለጹ፡-

ጦር መጣ ይላሉ እኔ ምን ቸገረኝ

እናቴም ልጅ የላት እኔም ወንድም የለኝ!

ወንድሞቻቸውን እና ሌሎች ታማኞቻቸውን በጦርነቱ ያጡት ደጃዝማች ባልቻ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ተመልሰው የሚሆነውን መጠባባቅ ጀመሩ፡፡ ጥቅምት 27 ቀን 1929 ዓ.ም የጠላት ጦር ደጃዝማች ባልቻ ወደሚኖሩበት በመዝለቅ በእሳቸው ላይ ዘመተባቸው፡፡ ከሁለት አሽከሮቻቸው ሦስት ሆነው ሲቀሩ ብዛት ያላቸው ጣሊያን ከበባቸው፡፡

በመጨረሻም ጣሊያኖቹ "እጅህን ስጥ መሳሪያህን ጣል” ሲሏቸው ደጃዝማች ባልቻ "እኔ እጄን የምሰጥ ፈሪ ሰው አይደለሁም፤ ትጥቄን አልሰጥም" ብለው የጣሊያኖችን አዛዥ ገድለው በራሳቸው ጥይት የራሳቸውን ህይወት አጠፉ።

በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩት ሻለቃ መስፍን ስለሺ ለንደን ለነበሩት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በጻፉት ደብዳቤ፣ “…የጠላት ጦር ደጃዝማች ባልቻ ወድሚኖሩበት በመዝለቅ በሳቸው ላይ ዘመተባቸው። ህዝቡ ከዳቸው፤ ወታደሮቻቸውም ለህይወታቸው ሲሉ ሸሹ። እሳቸው ደጃች ባልቻ እና ሁለት አሽከሮቻቸው፤ ከሳቸው ጋር ሶስት ሰዎች ብቻ ቀሩ። ያ ሁሉ የጣልያን ጦር ከበባቸው። ወዴትም መሄድ አልቻሉም።

በመጨረሻም አንድ ነጭ ፈረንጅ ወደጃች ባልቻ ዘንድ መጣ። ከዚያም… ‘ደጃዝማች ባልቻ ማለት አንተ ነህ?’ አላቸው። ደጃዝማቹም ‘አዎ እኔ ነኝ!’ ሲሉ፤ ፈረንጁ ‘በሉ ይማረኩ፤ ሽጉጥዎትንም ያስረክቡኝ’ አላቸው። ደጃዝማች ባልቻም ‘እኔ እጅ የምሰጥ ሰው አይደለሁም፤ ትጥቄንም አልሰጥህም!’ ብለው ሽጉጣቸውን አውጥተው፤ ነጩን የጣልያን ጦር መኮንን ገደሉት። ከዚያም በራሳቸው ሽጉጥ የራሳቸውን ህይወት አጠፉ። ከደጃዝማች ባልቻ ጋር አብረው የነበሩትም ወታደሮች ስቃይ ሳይበዛባቸው በየተራ ወደቁ።” በማለት በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

እነሆ የጀግና ውለታ የማይረሳው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆኖ ታሪካቸውን ሲዘክር ይኖራል፡፡ለክብራቸው መተሰቢያም ታላላቅ ቦታዎች በስማቸው ተሰይመዋል። ከነዚህም መካከል በሩስያውያን እርዳታ የተገነባው ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል፣ ደጃዝማች ባልቻ መንገድ፣ ደጃዝማች ባልቻ ትምህርት ቤት ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። ጀግኖች ሲፎክሩ እና ሲያቅራሩ ስማቸውን እየጠሩ፣ “ዘራፍ የባልቻ አሽከር!” ብለውላቸዋል።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top