ሰባተኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ተካሄደ

5 Mons Ago
ሰባተኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ተካሄደ

ሰባተኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም በአፍሪካ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራን መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ተካሂዷል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ክላቨር ጌት ፎረሙን በንግግር የከፈቱ ሲሆን፤ የተለያዩ ሀገራት ኃላፊዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተው ልምዳችውን አካፍለዋል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ክላቨር ጌት በመድረኩ ላይ፤ ኢኖቬሽን ለአፍሪካ የወደፊት እድል ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ፎረሙ የአፍሪካ አገራት መንግስታት እና የግሉ ዘርፍ የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች እና የአጀንዳ 2063 ለማሳካትና በጋራ ለመስራት ከዚህ ቀደም የጀመሩትን ውይይት እንዲቀጥሉ የማድረግ እና የማጎልበት ዓላማ እንዳለው ተገልጿል።

በአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ላይ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና ጎግል በአፍሪካ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማሳደግ እና ለማፋጠን የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል። 

የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ላይ የአፍሪካ አገራት ኃላፊዎች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋኒያን፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች እና የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል።

የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዘጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን፤ ፎረሙ የትምህርት ጥራትን በማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን አሉታዊ ተፅእኖ በመቅረፍ እና የምርታማነት አቅምን በማጎልበት የአፍሪካ አህጉርን አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

በወይንሸት ደጀኔ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top