የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ27ኛ መደበኛ ስብሰባው ያሳለፋቸው ውሳኔዎች

1 Mon Ago
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ27ኛ መደበኛ ስብሰባው ያሳለፋቸው ውሳኔዎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 27ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያሳለፋቸው ውሳኔዎች፡-

  1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ሀገራችን ያላትን የደን ሀብት በአግባቡ ለማልማት፣ ለመጠበቅ እና በዘላቂነት ለመጠቀም፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲሁም የካርበን ከምችትን ወደ አለም አቀፍ ግብይት ስርዓት ለማስገባት የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምከር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
  2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተፈረሙ 3 የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ ስምምነቶቹ ለዲጂታል መታወቂያ አካታችነትና አገልግሎት አሰጣጥ ፕሮጀከት ማስፈፀሚያ የሚውል የ300 ሚሊዮን ዶላር፣ ለትምህርትና ስልጠና ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ200 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለንግድ ሎጅስቲከስ ማሻሻያ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል የ9ዐ ሚሊዮን ዶላር ብድር የሚያስገኙ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱም ሁሉም ብድሮች ወለድ የማይታሰብባቸው፣ ብድሮቹን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጪዎች እንዲሁም ጥቅም ላይ ላልዋለው ገንዘብ 1.25% የአገልግሎት ከፍያ የሚከፈልባቸው፣ የ6 ዓመታት የችሮታ ጊዜ ያላቸው እና በ38 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ እንዲሁም ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ረቂቅ አዋጆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
  3. አክሎም ምከር ቤቱ ከጣሊያን መንግስት ጋር በተፈረሙ 2 ፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቶች ላይ የተወያየ ሲሆን የመጀመሪያው ስምምነት ለቦዬ ሐይቅና አካባቢው ዘላቂ ልማት ፕሮጀከት ማስፈጸሚያ የሚውል የ6.5 ሚሊዩን ዩሮ ብድር የሚያስገኝ፣ ሁለተኛው ስምምነት ለኢነርጂ ዘርፍ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ83.5 ሚሊዩን ዩሮ ብድር የሚያስገኝ ነው:: ብድሮቹ ከወለድ ነጻ ከመሆናቸውም በላይ የከ6 ዓመታት የአፎይታ ጊዜ ያላቸው በ30 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ መሆኑን እና ከአገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
  4. ሌላው ምከር ቤቱ የተወያየው ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትን በልማት ድርጅትነት ለማቋቋም የወጣውን ደንብ ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ከትባቶችን እና መድሃኒቶችን፣ በእንሰሳት ጤና ረገድ ለሚደረግ ምርምር የሚያገለግሉ ባዮሎጂካሎችንና ሪኤጀንቶችን እንዲሁም ተዛማጅ ግብአቶችን በራስ አቅም ለማምረት የተያዘውን አገራዊ ስትራቴጂ ማሳካት እንዲችል የኢንስቲትዩቱን ካፒታል ማሳደጊያ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም የኢንስቲትዩቱ የተፈቀደ ካፒታል ብር 2.6 ቢሊዮን እንዲሆን፣ ደንቡም በነጋሪት ጋዜጣ ከታተመበት ቀን ጀምሮ ስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
  5. በተጨማሪም የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት እና የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ተቋማት ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች የሚከፈሉ የአገልግሎት ከፍያዎችን ለመወሰን በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ላይ ምከር ቤቱ ተወያይቷል፡፡ ተቋማቱ የሚሰጡዋቸውን አገልግሎቶች ማስፋት፣ የአገልግሎታችውን የጥራት ደረጃ ማሻሻል፤ ብሎም የተጠቃሚውን ማህበረሰብ አቅም ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት ያወጡትን ወጪ በከፊል መሸፈን እንዲችሉ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ ደንቦች ተዘጋጅተው ቀርበዋል፡፡ ምከር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
  6. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ስራዎቻችን ከዘላቂ የልማት እና ብልጽግና ግቦቻችን ጋር እንዲተሳሰሩ፣ ለሰው ህይወት ቅድሚያ የሚሰጡ እንዲሆኑ ለማስቻል ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን፣ የህገ-መንግስታዊ ስርዓታችን እና ሀገራችን ያፀደቀቻቸውን ስምምነቶች ታሳቢ በማድረግ ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለምከር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት ከዛሬ የካቲት 16 ቀን 2016 ዓም ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
  7. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በይነ-መንግሥታዊ የልማት ባለሥልጣን (አጋድ) ማቋቋሚያ ማሻሻያ ስምምነትን ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በአባል ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ አካባቢያዊ እና ፖለቲካዊ ውህደት እንዲሁም የድንበር ተሻጋሪ ትበብርን በማፋጠን የአባል ሀገራትን ዘላቂ ልማት ማሳለጥ የሚገባ በመሆኑ የኢጋድ መመሥረቻ ስምምነት ማሻሻያ ጁን 12 ቀን 2023 በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ጸድቋል፡፡ ምከር ቤቱም በተሻሻለው የኢጋድ ማቋቋሚያ ስምምነት ላይ በሰፊው ተወያይቶ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
  8. በኢትዮጵያና በጆርዳን መንግስታት መካከል በስራ ስምሪት ዘርፍ የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ ለማጸደቅ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ ነው፡፡ ስምምነቱ በጆርዳን በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ እና ለወደፊትም ለሚሄዱ ኢትዮጵያውያን የመብት አከባበር ህጋዊ መሰረት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ በሁለቱ መንግሥታት መካከል የሚኖራትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በህዝብ ለህዝብ ደረጃ ለማጠናከርም እንደሚያስችል የታመነበት ስምምነት ማስጸደቂያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ስምምነት ላይ በሰፊው ተወያይቶ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
  1. በመጨረሻም ምከር ቤቱ የተወያየው የብሮሚን፣ የግራናይት፣ የድንጋይ ከሰል እና የደለል ወርቅ ማእድናት ልማትን የተመለከቱ 4 ረቂቅ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ ለምክር ቤቱ የቀረቡት ረቂቅ ስምምነቶች የኢንደስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማሟላት የተነደፈውን ስትራቴጂ በማሳካት፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ፣ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረከቱ፣ እንዲሁም ከአካባቢ ጥበቃ እና ከማህበረሰብ ተጠቃሚነት ረገድ የመንግስትን የፖሊሲ አቅጣጫ የተከተሉ ስምምነቶች መሆናቸውን በማረጋገጥ የማእድን ሚኒስቴር ስምምነቶቹን እንዲፈራረም እና ወደ ስራ እንዲገባ በሙሉ ድምጽ ይሁንታ ሰጥቷል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top