ድንገተኛ የፊት መጣመም ህመም እንዴት ይከሰታል?

1 Mon Ago
ድንገተኛ የፊት መጣመም ህመም እንዴት ይከሰታል?

በተለምዶ መጋኛ መታው፤መጋኛ ፊቱን አጣመመው ሲባል ሰምተን ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የድንገተኛ የፊት መጣመም ህመም በዘመናዊ ህክምና  የራሱ ማብራሪያ ያለው የበሽታ አይነት ነው፡፡

ድንገተኛ የሆነ የፊት መጣመም ወይም በህክምና አጠራሩ (bell's palsy) በአንድ በኩል የሚገኙ የፊት ጡንቻዎች መድከም፣መስነፍ ወይም መዛል ሲሆን የፊታችንን ቅርፅ የሚቀይር ከአንጎል ከሚነሱት 12 ነርቮች አንዱ የሆነው ሰባተኛው ነርቭ (facial nerve) ብግነት ወይም እብጠት ምክንያት የሚመጣ የነርቭ ህመም ነው።

ፊታችን ከጭንቅላታችን በሚነሱ ነርቮች አማካኝነት የእለት ተዕለት ተግባራትን ያከውናል። አብዛኞቹ ነርቮች የፊታችንን እንቅስቃሴ ይይዛሉ፣ ይቆጣጠራሉ።

ፊታችን ቀስ በቀስ ወይም በድንገት ሊጣመም እንድሚችል የህክምና ባለሞያዎቸ ያስረዳሉ። ይህ ችግር በማንኛውም የእድሜ ክልል ሊከሰት የሚችል ሲሆን፤ ፊታችንን የሚመግቡ ነርቮች ከጭንቅላታችን ሲወጡ በሚከሰት ጫና ወይም ጉዳት ሊከሰት ይችላል።

ህመሙ በአብዛኛው ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ወደ ነበረበት ለመመለስ ሳምንታት ወይም ወራት ይፈጃል ተብሎ ይታሰባል። የተወሰኑ ሰዎች ላይ ደግሞ እስከ ሀይወት ዘመን ሊቆይ ይችላል።

የበሽታው መንስኤዎች ምንድን ናቸው?

የድንገተኛ የፊት መጣመም ይህ ነው የሚባል ምክንያት እንደሌለው ይነገራል፡፡ አንዳንድ ጥናት አጥኚዎቸ እንደሚሉት በአንድ በኩል የሚገኘውን የፊታችንን ጡንቻ የሚቆጣጠረው ነርቭ ሲቆጣ ፣ ወይም እብጠት ሲኖረው ነው ብለው አሰቀምጠዋል። ይህም በተለይ በቫይረስ ኢንፌክሽን አማካኝነት ነው ተብሎ እንደሚታሰብ ይገልፃሉ።

አብዛኛውን ጊዜ ነፍሰጡር እናቶች፣ የላይኛው የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን፣ ስኳር፣ደም ግፊት እና ከመጠን በላይ ውፍረት ያለባቸው ሰዎች ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው ተብሎ ይታሰባል።

የበሽታው ምልክቶች

በዚህ በሽታ ላይ ድንገተኛ በሆነ መልኩ በአንድ በኩል ብቻ የፊት መድከም፣ መስነፍ፣ የፊት መውደቅ፣ ጉንጭን በአየር ለመሙላት መቸገር ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው፡፡

እንዲሁም መሳቅ፣ ፈገግ ማለት  እና ሌሎች የፊት እንቅስቃሴዎች ለማድረግ መቸገር፤ የፊት መደንዘዝ፣ የአንድ አይን መክደን አለመቻል፣ የምራቅ መዝረክረክ ፣ ለማፏጨት መቸገር ሌለች ምልክቶች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በግንባር መኮሳተር አለመቻል፣ የአፍ በአንድ በኩል መውረድ፣ ከጆሮ ጀርባ አና መንጋጭላ አካባቢ የህመም ስሜት መሰማት፣ የእራስ ምታት፣ ጣእም ለማጣጣም መቸገር፣ የእንባ እና የምራቅ መጠን መለወጥ በበሽታው ላይ የሚታዩ ሌሎች ምልክቶች ናቸው።

በሽታው በጊዜ ህክምና ካልተደረገለት የፊት ነርቭ በቋሚነት መጎዳት፣ የነርቭ ዘንጎች በትክክል አለማደግ፣ የአይን መድረቅ፣ የአይን ኢነፌክሽን እንዲሁም መታወር ድረስ ሊያደርስ እንደሚችል የህክምና ባለሙያች ይገልፃሉ።

ለድንገተኛ የፊት መጣመም የሚሰጠው ህክምና

ለዚህ በሽታ የፊዚዮቴራፒ ህክምና እጅግ ጠቃሚ የሆነ የህክምና አይነት ሲሆን፤ ይህም የተለያዩ የፊት ላይ እንቅሰቃሴዎች እና የፊት ጡንቻ ስፖርቶች በማድረግ የደነዘዙ የፊት ጡንቻዎችን ወደ ነበሩበት ለመመለሰ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እንዲመጣ ያስችላሉ።

ሰዎች ከምንም በፊት ግን ይህን አይነት ችግር ሲመለከቱ  ወዲያውኑ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ መታየት ቢችሉ የህክምና ባለሞያዎች ቀዳሚ ምክር  ነው። 

በሜሮን ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top