ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ማሰልጠኛ ተቋምን ጎበኙ

6 Mons Ago 574
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ማሰልጠኛ ተቋምን ጎበኙ

በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራው ልዑክ የአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ማሰልጠኛን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።

በመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ስር ካሉት አንጋፋ የስልጠና ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ማሰልጠኛ ብቁ የሜካናይዝድ ሙያተኞችን በማፍራት ረገድ አቅሙን እያሳደገ የመጣ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ማሰልጠኛው በመስክና በክፍል ውስጥ እየሰጠ ያለውን የስልጠና ሂደት አስመልክቶ ለልዑካን ቡድኑ ገለፃ ተደርጓል።

ማሰልጠኛው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሰለጠኑት አሰልጣኞቹ አማካይነት ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የሜካናይዝድ ሙያተኞችን በብቃትና በጥራት እያሰለጠነ መሆኑን ተገልጿል።

በክፍል ውስጥ ከሚሰጠው ስልጠና በተጨማሪ ሰልጣኞች በተለያየ የመሬት ገፅ ላይ በቋሚና በተንቀሳቃሽ ኢላማዎች ላይ ልምምድ የሚያደርጉበት የመስክ ስልጠና ወረዳዎችም በልዑካን ቡድኑ ተጎብኝተዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር  ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተደረገላቸውን ገለፃ መሰረት ማሰልጠኛው ለሚያከናውነው የመማር ማስተማር ሂደት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

በጉብኝቱ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ይመር መኮንን ጨምሮ ጀነራል መኮንኖችና ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ከሃገር መከላከያ ሠራዊት ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top