ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ላላት ኢትዮጵያ ባህር በር ማግኘት የህልውና ጉዳይ ነው - ምሁራን

1 Mon Ago
ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ላላት ኢትዮጵያ ባህር በር ማግኘት የህልውና ጉዳይ ነው - ምሁራን

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት “የባህር በር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እና ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊ ምሁራን እንደገለጹት የባህር በር ያላቸው ሀገራት በኢኮኖሚው፣ በዲፕሎማሲና በውጭ ግንኙነት በኩል የላቀ ተሰሚነት ይኖራቸዋል።

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ መሐመድ ኢብራሂም፤ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ላላት ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የህልውና ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው ነው ብለዋል፡፡

በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚሠማሩ ባለሃብቶች ቀዳሚ ምርጫቸው የባህር በር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አሁን የምንገኝበት ዓለም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ውድድር የበዛበት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ውድድሩን አሸንፎ ለመውጣት ወደብን የመሳሰሉ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ መሳሪያዎች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት።

ሀገሪቱ የባህር በር ለማግኘት የሄደችበት የሰጥቶ መቀበል መንገድ የቀጠናውን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ መሆኑን በማከል፡፡

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አስራት ኤርሞሎ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ የምታወጣው ዶላር ትልልቅ ፋብሪካዎችን መገንባት እንደሚያስችል አንስተዋል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ቀውስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከባህር ባርና ወደብ አለመኖር ጋር ይገናኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት እየሄደችበት ያለው መንገድ የሚበረታታና ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በተለይም በቀጣናው ያለውን ተሰሚነት በማሳደግ በውጭና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንደሚያሳድግ አብራርተዋል፡፡

የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በውጭ ሃይሎች ጫና የሚወድቁበት አጋጣሚ እንደሚኖር የተናገሩት ደግሞ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዲን እና መምህር ኪዳኔ ደያሳ ናቸው፡፡

የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ አቅም እና የባህር በር ተጽዕኖ ከመፍጠር አንጻር የማይነጣጠሉ ጉዳዮች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top