የዓድዋው ችሎት

2 Mons Ago
የዓድዋው ችሎት

የካቲት 25 ቀን 1888 ዓ.ም እነሙንጣዝ፣ቡልቅ ባሻ እና ባሻ ብዙቅ ላይ ምን ተወሰነ?

በወራሪው የጣልያን ጦር ሠራዊት ላይ ጀግኖች አባቶቻችን ታሪካዊውን ድል የካቲት 23 በተቀዳጁ ማግስት፤ የካቲት 24 እና 25 ዐፄ ምኒሊክ የሟቾችን አስከሬን በማስለቀም እና በማስቀበር የሁለት ቀናት ጊዜ ካሳለፉ በኋላ፤ የካቲት 25  1888 ዓ.ም ችሎት ተሰይሞ እንደነበር የሚነግሩን የታሪክ ፀሐፊው ተክለፃዲቅ መኩሪያ ዐፄ ምኒሊክ በተሰኘው መፅሀፋቸው የዓድዋውን ችሎት ውሎ ተርከውታል።

መፅሐፉን እያጣቀስን የዓድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ የዓድዋውን ችሎት፣ ፍርዱን እና ተመሳሳይ ወንጀል በሥራ ላይ ባለው ሕጋችን ሚያስከትለውን ቅጣት እናያለን።

የክሱ መነሻ

በዓድዋ ጦርነት ጀግኖች አባቶቻችን የተዋጉት ባሕር አቋርጦ ከመጣው የጣልያን ጦር ጋር ብቻ አልነበረም። ጣልያን አሰብን በ1879 ዓ.ም በግዢ፤ ምፅዋን ደግሞ በ1885 ዓ.ም በወረራ ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ፤ ከሀገር ተወላጆች ወታደርነት እየመለመለ፣ መለዮ ኮትና ሱሪ እያሰፋ እና የወር ቀለብ እየሰጠ ልዩ ልዩ ያገር ተወላጅ ጦር አቋቁሞ ነበር።

እነዚህንም ወታደሮች ሁልጊዜ አዛዥ ጣሊያን ሲሆን ከመሀከላቸው እየመረጠ ‘‘ሙንጣዝ፣ቡልቅ ባሻ እና ባሻ ብዙቅ’’ እያለ እየሾመ በአስፈለገው ጊዜ ከነራስ አሉላ እና ከነራስ መንገሻ ጋር ሲያዋጋቸው ኖሯል።

በዓድዋ ጦርነት ላይም ግንባር ቀደም ሆኖ ከጣሊያኖቹ ጋር ወገኑን የወጋው የሀገር ተወላጅ (ባንዳ) ቁጥሩ 6 ሺህ ይደርሳል። ከነዚህም ውስጥ አንዳንድ የሱዳን ተወላጆች ቢኖሩም፤ብዙዎቹ ከሐማሴን፣ከሠራዬ እና ከአካለ ጉዛይ ተሰባስበው የሰንአፌን፣የኮዐቲትን፣የአምባ አላጌን እና የመቀሌን ጦርነት የተካፈሉ ነበሩ።በጦርነቶቹ ላይም በወገን ጦር ላይ ብዙ ጉዳት አድርሰው ነበር።

ዐፄ ምኒሊክ ከአላጌ ጦርነት በኋላ በትግሬ ግዛት እንደገቡ "ከጠላቴ ጋር ሆነህ የወጋኸኝ ያገር ተወላጅ ወታደር አይቀጡ ቅጣት እቀጣሀለሁ እርስትህን እነቅልሀለሁ!" የሚል ዐዋጅ በማስነገራቸው በዚህ መሰረት እነራስ ስብሀት መጥተው ገቡላቸው።

 በዓድዋ ጦርነት ላይም ባሻ ባዙቆቹ ምንም ገንዘባቸውን ብንበላ ሀገራችንን እና ንጉሳችንን አንወጋም ብለው አስቀደመው ሸሹ ።አላጌ ላይ የተማረከውንም የጣልያን ባንዳ ሠራዊት ምረውት ነበር።

የካቲት 25 ቀን 1888 ዓ.ም ችሎት የተሰየመውም በዓድዋ በጦርነት ላይ ከጠላት ጎን ተሰልፈው ወገናቸውን  ከተዋጉት ባንዳዎች ከሞቱት እና ካመለጡት ውጭ የተማረኩትን 1ሺህ 200 የሀገር ተወላጅ የጠላት ወታደሮችን ለመዳኘት ነበር።

የተሰጠው ፍርድ

ንጉሱም ታላላቅ ባለሟሎቻቸውን ሰብስበው በነዚህ የገዛ ወገናቸውን ከድተው ከጠላት በማበር የወጉ ሰዎች ላይ የሚሰጠውን ፍርድ ቀለል እንዲልና በእስር ቅጣት ብቻ እንዲታለፉ አስበው ነበር። በዚሁ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ፣አቡነ ማቲዎስ፣ራስ ወሌ እና ከባንዳዎቹ ጋር ሲዋጉ የኖሩት ራስ መንገሻ እና ራስ አሉላ አይሆንም ብለው በዘመኑ በሥራ ላይ የነበረው ሕግ ፍትሐ ነገስት በሚያዘው መሰረት ከፍ ያለ ቅጣት እንዲቀጡ አመለከቱ።

በተለይም ራስ መንገሻ የነዚህ ከዳተኞች ‘እጅና እግራቸው ይቆረጥልኝ’ ብለው ለዐፄ ምኒሊክ አጥብቀው አቤት አሉ።ከብዙ ክርክር በኋላም አብዛኛው መኳንንት የምኒሊክን የርህራሄ ቀላል የእስር ቅጣት ሳይሆን የእቴጌን እና የሌሎቹን ታላላቅ መኳንንት ሀሳብ በመደገፉ ሀገራቸውን የካዱና ወገናቸውን የወጉ ናቸው እና ፍትሐ ነገስቱ "ሀገሩን የከዳ ቀኝ እጅና ግራ እግሩ ይቆረጣል" ስለሚል ይሄው ቅጣት ተፈፀመባቸው።

የፍርድ ሂደቱ ይካሄድ የነበረው ገና የሟቾች አስክሬን እንኳን በወጉ አርፎ ባልተጠናቀቀበት ጊዜ ስለነበር፤ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ስላልነበር ከጦርነቱ የተረፉት ወታደሮቸና መኳንንትም አለቆቻቸው፣ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው የሞቱባቸው ሁሉ "ይቆረጡ ይቆረጡ!" እያሉ ያውኩ ስለነበር ባንዳዎቹ ላይ ለተፈፀመባቸው ቅጣት የራሱን አስተዋፅኦ አበርከቷል።

ይህ አይነቱ ቅጣት የጣልያን ምርኮኞችም ሆነ የሱዳን ቅጥረኛ ተዋጊ ምርኮኞች ላይ አልተፈፀመም ነበር።ለዚህም መሰረቱ "ያገር ተወላጅ ወታደሮቹ ወገናቸውን የከዱ ሲሆኑ እነዚያ ጣልያን እና ሱዳኖቹ ግን መንግስታቸው አዟቸው ነው። አይፈረድባቸውም!" የሚል ነበር።

የጣልያን ምርኮኞች ተገቢው እንክበካቤ እየተደረገላቸው ቆይተው የዕርቅ ስምምነት ከተደረገ በኋላ 1ሺህ148 ምርኮኞች በነፃ ተለቀው በግንቦት ወር 1889 ዓ.ም ሀገራቸው ገብተዋል።

በሥራ ላይ ያለው ሕጋችንስ ስለ ሀገር መክዳት ምን ይላል?

በነገራችን ላይ በሥራ ላይ ባለው የወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 251 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሀገራችን በጦርነት ላይ እያለች ወይም በከፊል በተወረረችበት ጊዜ፤ የጠላትን ዓላማ ለማሳካት በምክርም ሆነ በተግባር የደገፈ እና በአንቀፁ ስር በተዘረዘሩት የተለያዩ መንገዶች ጠላትን የረዳ ከ20 ዓመት ከማይበልጥ ፅኑ እስር አንስቶ ነገሩ ከባድ ከሆነ ደግሞ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት እንደሚቀጣ ይደነግጋል።

እንኳን ለ128ኛው የዓድዋ ድል በዓል አደረሰን!


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top