ኅብረተሰቡ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተዋወቁ መድኃኒቶችን ከመጠቀም ሊቆጠብ ይገባል፦ የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለስልጣን

2 Mons Ago 545
ኅብረተሰቡ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተዋወቁ መድኃኒቶችን ከመጠቀም ሊቆጠብ ይገባል፦ የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለስልጣን
ዓለም እየተጓዘች ባለችበት ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት ውስጥ ከዕለት ወደ ዕለት የሚከናወኑ ተግባራት ዘመኑ በፈጠራቸው ቴክኖሎጂዎች ላይ ጥገኛ ሆነዋል።
 
በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት፤ በሰዎች ዘንድ ያለው ማኅበራዊ መስተጋብር እጅ ላይ ባለ ስልክ እና ሌሎች አማራጮች ላይ እንዲወድቅ ሆኗል።
 
አሁን አሁን ምርቶችን በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች እያስተዋወቁ መሸጥ እየተለመደ መጥቷል።
 
ይህ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚከናወን የንግድ እንቅስቃሴ፤ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳት እንዳለውም ብዙዎች ይናገራሉ።
 
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተጠቃሚዎች ላይ ከፍተኛ የጤና ጉዳት የሚያደርሱ መድኃኒቶች፤ በፌስቡክ፣ቴሌግራም፣ ቲክቶክ እና በሌሎችም መተግበሪያዎች ላይ ሲተዋወቁ እየተስተዋለ ነው።
 
ለመሆኑ በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዋወቁ የሚሸጡ መድኃኒቶች ሕጋዊ ናቸው ወይ? ሲል ኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለስልጣንን አነጋግሯል፡፡
 
በባለስልጣኑ የመድኃኒቶች የጥራት ደረጃ ባለሙያ የሆኑት አቶ ፍቅሬ ወንድሙ፤ ማንኛውንም መድኃኒት በማኅበራዊ ሚዲያ እንዲተዋወቅ እና እንዲሸጥ የምንሰጠው ፈቃድ የለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
 
ማንኛውንም መድኃኒት በማኅበራዊ ሚዲያ ማስተዋወቅ እና መሸጥ እንደማይቻል የገለጹት ባለሙያው፤ ነገር ግን ይሄንን ወደ ጎን በማለት በተለያዩ አካባቢዎች እየተዋወቁ እና እየተሸጡ ያሉ መድኃኒቶች ምንም ዓይነት እውቅና እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
 
መድኃኒቶች መተዋወቅ ያለባቸው በተቋሙ መመሪያ ብቻ መሆን እንዳለበትም ነው ባለሙያው የገለፁት፡፡
 
አቶ ፍቅሬ በማኅበራዊ ሚዲያ መድኃኒቶችን የሚያስተዋውቁ እና የሚሸጡ አካላት ምንም ዓይነት ፈቃድ የሌላቸው በመሆናቸው ከዚህ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
 
በተጨማሪም ህብረተሰቡ መድኃኒቶችን ከማኅበራዊ ሚዲያ አይቶ ገዝቶ መጠቀም እንደማይገባውም አስታውቀዋል፡፡
 
ተቋሙ ይሄን መሰል ተግባራትን ለመቆጣጠር በተለያየ መልኩ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ፍቅሬ ገልጸዋል፡፡
 
በተስሊም ሙሀመድ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top