ሁሉም የመንግሥት አመራር የሕዝብን ችግር የሚፈታ ተምሳሌታዊ ተግባር ማከናወን አለበት - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

2 Mons Ago 708
ሁሉም የመንግሥት አመራር የሕዝብን ችግር የሚፈታ ተምሳሌታዊ ተግባር ማከናወን አለበት - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

የሁሉም የመንግሥት አመራር የሕዝብን ችግር የሚፈታና የአገርን ብልፅግና የሚያረጋገጥ የጋራ ግብን ለማሳካት ተምሳሌታዊ ተግባር መፈጸም እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ። 

የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የመንግሥት የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና አስተዳደራዊ ዘርፎች አፈጻጸም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና የተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል።

በግምገማውም ባለፉት ወራት እንደ አገር በዓመቱ ለማሳካት የታቀደውን የ7 ነጥብ 9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማሳካት እንደሚቻል አመላካች ውጤቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፉ መገኘታቸው ተገልጿል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በግምገማው ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት፤ ባለፉት ወራት በሁሉም ዘርፍ አበረታች ውጤቶች ቢገኙም አሁንም ትኩረት የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ።

የተቋማት ቅንጅት ማነስ፣ የጋራ ግብ አለመያዝና የአገልጋይነት መንፈስ ደካማ መሆን በቀጣይ ሊሰራባቸው ከሚገቡ አንኳር ጉዳዮች መካከል መሆናቸውንም ነው ለአብነት ያነሱት።

በመሆኑም በቀጣይ አገራዊ ግቡን ለማሳካት ተቋማዊ ቅንጅትን ማጠናከር፣ እቅዶችን ከአገራዊ ግቡ ጋር ማናበብና የካፒታል ፕሮጀክቶች ተፈጻሚነት ማረጋገጥ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ሁሉም አመራር የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥን የጋራ ግብ አድርጎ ሊሠራ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት አገር ናት ያሉት አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ መንግሥት ድፍረትን የሚጠይቁና የአገርን ጉዞ ቀና የሚያደርጉ የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም አመላክተዋል። 

ይህንንም ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ሕገ-ወጥ አሰራርና ሌብነትን መታገል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ተቋማት ለሪፖርት ተዓማኒነትና ውጤት መርነት ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው በማንሳት፥ የተቋማት ምዘና ውጤትን የሚለካ መሆን እንዳለበትም ነው የተናገሩት። 

ባለፉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበውን ውጤታማነት በኢንዱስትሪና በማዕድን ዘርፎችም ለመድገም የሁሉንም የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።   

ለዚህም መንግሥት ለምርታማነት መጨመር፣ ለግብዓት አቅርቦት መጠናከርና በገበያው ውስጥ የአገር ውስጥ ምርትን ቅድሚያ እንዲያገኝ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የገንዘብና ፖሊሲን የማጥበቅ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንዲያም ሆኖ ምርታማነትን ማሳደግና የግብይት ሥርዓቱን መስመር ማስያዝም የሁሉም ተቋማት ኃላፊነት በመሆኑ በዚህ ረገድ የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

እንደ አገር በኢኮኖሚ ዘርፍ ካሉ አበረታች ሥራዎች ጎን ለጎን በማኅበራዊና አስተዳደራዊ ዘርፎችም ጥሩ ጅምሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ይህም መጠናከር አለበት ነው ያሉት።

አገሪቷን በሁለንትናዊ መልኩ የተሻለች ለማድረግ አመራሩ ሌት ተቀን መሥራት እንዳለበትም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ታች ወርዶ የሚተጋ እንዲሁም ለሰራተኛው አርዓያ የሚሆን አመራር እንደሚያስፈልጋት አንስተው ከዚህ አኳያ የመንግሥት ኃላፊነትን የተረከበ አመራር ሁሉ የሕዝብን ችግር የሚፈታ ተምሳሌታዊ ተግባር ማከናወን አለበት ብለዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top