የስፖርት ውርርድ ቁማር ራስን እስከማጥፋት የሚያደርስ ሥነ- ልቦናዊ ጫናን ያስከትላል፡- የሥነ-ልቦና ባለሙያ አቶ ዳዊት ላቀው

8 Mons Ago 1069
የስፖርት ውርርድ ቁማር ራስን እስከማጥፋት  የሚያደርስ ሥነ- ልቦናዊ ጫናን ያስከትላል፡- የሥነ-ልቦና ባለሙያ አቶ ዳዊት ላቀው
በእግር ኳስ አማካኝነት የሚደረግ የስፖርት ውርርድ ወይም ቤቲንግ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።
 
በዚህ ውርርድ ውስጥ ለእግር ኳስ ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው ታዳጊዎች እና ወጣቶች ዋነኛ ተሳታፊዎች እንደሆኑም ይነገራል፤ ይህ የውርርድ ወይም ቤቲንግ በአሁኑ ጊዜ በበርካቶች ዘንድ ወደ ሱስነት እየተሸጋገረ መምጣቱን ብዙዎች ይገልጻሉ።
 
የስፖርት ውርርዱ ብዙ ዓይነት ሥነ- ልቦናዊ ጫናዎች ያደርሳል የሚሉት ኢቢሲ ሳይበር ያነጋገራቸው የሥነ- ልቦና ባለሙያው አቶ ዳዊት ላቀው ናቸው።
 
እንደ ባለሙያው ገለጻ፤ ውርርዱ ቁማር በመሆኑ ሰዎች አዲስ ባሕሪ እንዲያመጡ ወይም እንዲለምዱ ያደርጋል፤ይህንንም ተከትሎ የሚፈጠረው አዲስ ባሕሪ ሰዎችን ሱስ ውስጥ ሊከት ይችላል።
 
አንድ ሰው ሱስ ውስጥ ከገባ ብዙ ዓይነት ችግሮች በሕይወቱ ይከሰታሉ የሚሉት አቶ ዳዊት፤ከሱሱ ውጭ ሌላ ደስታን የሚፈጥር ነገር በሕይወት ውስጥ ማጣት አንደኛው መገለጫ እንደሆነ ይናገራሉ።
 
የስፖርት ውርርዱ ሱስ ወደ መሆን ደረጃ ከፍ ሲል ንብረትን፣ ስራን እና ትዳርን እስከ ማጣት እንደሚያደርስም ይገልጻሉ።
 
በቤቲንግ ሱስ የተያዙ ሰዎች ማኅበራዊ ሕይወታቸው እንደሚቀንስ የገለጹት ባለሙያው፤ ለከፍተኛ ድብርት፣ጭንቀት እና የመገለል ስሜትም እንደሚዳረጉ ያብራራሉ።
 
ከዚህም አለፍ ሲል የአዕምሮ ቀውስን በመፍጠር፤ራስን እስከማጥፋት የሚያደርስ ሥነ- ልቦናዊ ጫናን እንደሚያስከትልም ነው የሚገልጹት።
 
በቤቲንግ ቁማር ሱስ የተያዘ ሰው ከሱሱ ለማገገም በርካታ መፍትሔዎች ይኖሩታል ያሉት አቶ ዳዊት፤በቅድሚያ ግን በሱስ ውስጥ እና በችግር ውስጥ መሆኑን ማመን አለበት ብለዋል።
 
ከችግሩ ለማገገም የተለያዩ የሥነ- ልቦና ድጋፎች እና ሕክምናዎች እንዳሉት የጠቆሙት ባለሙያው፤ በዚህ ሱስ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የሥነ- ልቦና ባለሙያ ማማከር እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ።
 
በተስሊም መሐመድ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top