የራስ ያልሆነን ገንዘብ ስለ መውሰድ

1 Mon Ago
የራስ ያልሆነን ገንዘብ ስለ መውሰድ

መጋቢት 6 2016 ዓ.ም ምሽት ላይ የኢትዮጽያ ንግድ ባንክ የሲስተም ማዘመኛ በማካሄድ ላይ እያለ በተፈጠረ ክፍተት የገንዘብ መጠኑ በመጣራት ላይ ያለውን የገንዘብ መጠን በሂሳባቸው ውስጥ በቂ ገንዘብ እንደሌለ እያወቁ ክፍተቱን ተጠቅመው በኤቲኤም ካርድና በሞባይል ባንክ የሂሳብ ማንቀሳቀሻ መንገድ ወደ ሌላ ባንክ ተላለፎ እንደተወሰደበት ገልጷል።

በዚህ ድርጊት የተሳተፉትም አብዛኞቹ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ሰሞኑን ክስተቱ ብዙዎችን ሲያነጋግር ሰንብቷል።

ለመሆኑ ይህን መሰል የራስ ያልሆነ ገንዘብን የመውሰድ ተግባር በሕግ ዓይን እንዴት ይታያል ምን አይነት ተጠያቂነት ያስከትላል የሚሉትን ነጥቦች እንመልከት።

ባንኮችና የሂሳብ አስቀማጭ ደንበኞቻቸው

በባንኮችና የሂሳብ ቋት በባንኮቹ የከፈቱ ደንበኞቻቸው መሀል ያለው ግንኙነት በዋነኛነት የሚመራው በገንዘብ ማስቀመጥ የአደራ ውልና ሂሳቡን ሲከፍቱ ከገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞቻቸው ጋር ባንኮቹ በሚገቡት የሂሳብ ቋት ውል ነው።

በዚህ ውል መሰረትም ከባንኩ ጋር የተለየ የውል ስምምነት ከሌለ በስተቀር ማንኛውም ባለሂሳብ ሂሳቡ ውስጥ ከሚገኘው የገንዘብ መጠን በላይ ማውጣት አይችልም። በመሆኑም በወቅቱ የተከሰተውን ክፍተት ተጠቅመው በሂሳባቸው ውስጥ ካለው የገንዘብ መጠን በላይ ወጪ ያደረጉ ወይም ወደ ሌላ ሂሳብ ያስተላለፉ ሰዎች ይህን የሂሳብ ቋት ውል ጥሰዋልና የሂሳብ ቋታቸውን የሚያንቀሳቅሱበትን ስምምነት በመጣስ የወሰዱትን ገንዘብ ለባንኩ የመመለስ ግዴታ አለባቸው።

አላግባብ የተከፈለ ገንዘብ

በወቅቱ በባንኩ የክፍያ ሲስተም ላይ በተፈጠረው እክል በሂሳባቸው ውስጥ ካላቸው ገንዘብ በላይ ወጪ ያደረጉ ወይም ገንዘብ ያስተላለፉ ሰዎች ገንዘቡን ያገኙት ወይም ማስተላለፍ የቻሉት መብቱ ሳይኖራቸው በመሆኑ አላግባብ  ገንዘቡን ወጪ አድርገዋል ወይም ወደ ሌላ ሂሳብ አስተላልፈዋል።

ያላግባብ የተከፈለ ክፍያ የሚመለሰው ደግሞ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ቁጥር 2164 መሰረት ነው። አንድ ሰው መክፈል የሌበትን ገንዘብ ከከፈለ የከፈለውን ሰው እንዲመለስለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡

ገንዘብ ተቀባዩ እምነትን በሚያጎድል መንገድ ክፍያውን ከተቀበለ የማይገባውን ገንዘብ በመቀበሉ የተነሳ ዋናውን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከፋዩ የማይገባውን ገንዘብ ከከፈለበት ቀን ጀምሮ የሚታሰብ ሕጋዊ ወለድን ወይም ገንዘቡ ያስገኘውን ፍሬም ጭምር እንዲከፍለው የማይገባውን ክፍያ የከፈለ ሰው አስከፋዩን መጠየቅ ይችላል።

በመሆኑም ባንኩ ገንዘቡን በኤቲኤም ወጪ ያደረጉትንም ሆነ ወደ ሌላ ባንክ ያስተላለፉትን ግለሰቦች ዋናውን ገንዘብ፣ ሕጋዊ ወለዱንና በገንዘቡ የተፈራ ፍሬ ካለ እንዲሁም ለክሱ ያወጣውን ወጪ ጨምሮ በፍትሐ ብሔር ከሶ ማስከፈል ይችላል።

 

የወንጀል ኃላፊነት

በወቅቱ የተከሰተውን ክፍተት በመጠቀም በሂሳባቸው የሌለውን ገንዘብ በኤቲኤም ወጪ የማድረግ ወይም ወደ ሌላ ሂሳብ የማስተላለፍ ድርጊት የሌላውን ሰው ገንዘብ ወይም ንብረት ለራስ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም ለማዋል ያለ ባለቤቱ ፍቃድ ወይም በሕገወጥ መንገድ የመውሰድ የስርቆሽ ወንጀል ነው።

የተከሰተው የሲስተም ክፍተት ተጠቅመው የሌላቸውን ገንዘብ ከሂሳባቸው በማውጣት ወይም በማስተላለፍ ለግል ጥቅማቸው ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም ገንዘቡን ያዋሉ ሰዎችን በተመለከት የወንጀል ሕግ አንቀፅ 690 በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ እንደሚቀጡ ይደነግጋል። 

የወንጀሉን አፈፃፀም መንገድ ሲያስቀምጥም በስህተት ወይም ባልታሰበ ሁኔታ ከባለ ሀብቱ ፍቃድ ውጭ የሚገኘውን ነገር ለራሱ ወይም ከሌላ ያደረገ ሰውን ሚቀጣበት ድንጋጌ መሆኑን ይገልፃል።

ገንዘቡን ያወጡት ሰዎች በባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ ስርዓት ውስጥ የተከሰተውን ስህተት ወይም የገንዘብ አላላክና አወጣጥ መቆጣጠሪያ መንገድ ላይ ያጋጠመውን ድንገተኛ ክፍተት በመጠቀምና ገንዘቡ እንደሌላቸው እያወቁ በመሆኑ በተራ ስርቆሽ ወይም በዚህ አንቀፅ ስር ድርጊቱ በወንጀል ያስጠይቃቸዋል።

የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን በተመለከተ

ማንኛውም ዩንቨርስቲ የተማሪዎች የስነምግባር መተዳደሪያ ደንብ አለው። በዚህ ደንብ ላይ ለዘለቄታው ከትምህርት ገበታ እስከመሰናበት ከሚያደርሱ ጥፋቶች ውስጥ አንዱ ደግሞ በዩንቨርስቲው፣ በተማሪዎችና በግቢው ማህበረሰብ ንብረት ላይ የሚፈፀም ስርቆት በመሆኑ ዩንቨርቲዎቹም ተገቢውን ማጣሪያ አድርገው በተማሪዎች ስነምግባር ደንባቸው መሰረት ተገቢውን  አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ።

ለማንኛውም ያራስ የልሆነ ነገር የራስ አይደለምና በማንኛውም አጋጣሚ ቢሆን መውሰድ ወይም ለራስ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም ማዋል  ሕሊናዊ ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ተጠያቂነትም እንደሚያስከትል ሊዘነጋ አይገባም።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top