የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ

1 Mon Ago 681
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ስብሰባው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅን መርምሮ አፅድቋል፡፡
 
አዋጁ መንግስት የቤት አቅርቦትን ፍላጎት ለማሟላት እያደረገ ያለውን ጥረት፤ በሀገሪቱ ከተሞች የሚስተዋለውን ያልተረጋጋ እና ፍትሐዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ዋጋ አቅም ያገናዘበ ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ብሎም የአከራይ ተከራይ መብትን ለማስጠበቅ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተገልጿል።
 
በአዋጁ መሠረት አንድ ተከራይ ቤት ተከራይቶ ውል ከፈፀመ በኋላ ለሁለት ዓመት የቤት ኪራይ መጨመር እና ቤት ማስለቀቅ አይቻልም ተብሏል።
 
ተከራይ ቤቱን ከጎዳ እና ሌሎች አዋኪ ተግባራትን ከፈፀመ ግን በአዋጁ አንቀፅ 16 መሠረት ቤቱን ለመልቀቅ እንደሚገደድም ተደንግጓል።
 
ወደፊት ለሚደረግ ጭማሪ አሁን ላይ ያለው የኪራይ ዋጋ መሠረት ተደረጎ በመንግሥት የሚሰላ እንደሚሆንም በአዋጁ ተገልጿል።
 
ለቤት ኪራይ የሚሆን አዲስ ቤት የገነቡ አካላት እንደማበረታቻ ለ4 ዓመት ያህል በድርድር ዋጋ ማስቀመጥ የሚችሉ ሲሆን፤ ከዛ በኋላ ግን አዋጁ ተፈፃሚ እንደሚሆንባቸው ተገልጿል።
 
ለዚህ አዋጅ ተፈፃሚነት ምዝገባው በቀጣይ ባሉት 3 ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መስራታቸውም ተገልጿል።
 
ውል አለማስመዝገብ አስተዳደራዊ ቅጣት የሚያስከትል መሆኑ ተገልፆ፤ እስከ 3 ወር የሚደርስ የቤት ኪራዩን ዋጋ ያስቀጣልም ተብሏል።
አዋጁ በርካታ አዳዲስ አሰራሮችን ያካተተ ሲሆን ያከራይንም ሆነ የተከራይን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ህብረተሰቡ መብቱን እና ግዴታውን በማወቅ ለተፈፃሚነቱ እንዲተባበር ጥሪ ቀርቧል።
 
በሰለሞን ከበደ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top