ታላቅነት በጥረት እንደሚገኝ ያስመሰከረው - ሙሉቀን መለሰ

17 Days Ago
ታላቅነት በጥረት እንደሚገኝ ያስመሰከረው - ሙሉቀን መለሰ

ገና የ13 ዓመት ታዳጊ ሳለ ሙዚቃን የጀመረው የቀድሞው ድምፃዊ በ1958 ዓ.ም በፓትሪስ ሉሙምባ ምሽት ክለብ ፈጣን ኦርኬስትራን ተቀላቅሎ በመግባት ለሁለት ዓመታት ያህል መሥራት ችሏል።

የሙዚቃ ድርሰት ሲመርጥ በጣም የተለየ ችሎታ እንዳለው ይነገርነታል፡፡ በዚህ ምክንያትም እንደ ዓለምፀሐይ ወዳጆ እና ተስፋዬ ለሜሳ የሚመቹት የሉም፡፡

ተስፋዬ አበበ (ፋዘር)፣ ይልማ ገብረ አብ፣ አበበ መለሰ፣ ሰለሞን ተሰማ፣ ኩኩ ሰብስቤ እና ሌሎችም ግጥም እና ዜማ ቢሰጡትም፣ ግጥሞቹን እና ዜማዎቹን አንጥሮ የሚለይበት የራሱ ልዩ ተሰጥኦ አለው፡፡

በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ሬዲዮ እሁድ ጧት ፕሮግራም ላይ ባደረገው ቆይታ፣ "ለትዝታ ሙዚቃ ልዩ አመለካከት አለኝ፤ ፍቅር ውስጥም ትዝታ ስላለ ማለት ነው፤ እኔ ሙዚቃን ስሠራ በራሴ ቀለም ነው የምሠራው፤ ይህ ደግሞ ተወድዶልኛል፤ ባይወደድልኝ ኖሮ አድማጭ አላገኝም ነበር" ብሏል፡፡

እናቱ በልጅነቱ በመሞታቸው ምክንያት የሰው ፊት በማየቱ ይመስል "እናቴ ስትወልደኝ መች አማከረችኝ" የሚለው ዘፈኑ የተለየ ስሜት ይሰጣል፡፡

ሙሉቀን መለሰ በቀድሞው ጎጃም ጠቅላይ ግዛት አነደድ ወረዳ ዳማ ኪዳነ ምሕረት በምትባል መንደር በ1946 ዓ.ም ነው የተወለደው። አስር ዓመት ሲሆነው እናቱ ስለሞቱ አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩት አጎቱ እንዲማር ብለው የወሰዱት ሲሆን፣ ኮልፌ ጳውሎስ ትምህርት ቤት ገብቶ መማር ጀመረ።

በዚህ መሀል የአጎቱ ቤት ስላልተመቸው ከቤት ወጥቶ ኮልፌ ህጻናት ማሳደጊያ ገባ፡፡ የተቋሙ አስተዳዳሪ ይወዱት ስለነበር ‘ኤልቪስ’ ይሉት እንደነበረ ከስብሐት ገ/እግዚአብሔር ጋር በ1973 ዓ.ም ‘ፀደይ መጽሔት’ ላይ ባደረገው ቃለመጠይቅ ላይ ተናግሯል።

ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር ስለነበረው ከትምህርቱ ጎን ለጎን በልጆች ማሳደጊያው አካባቢ በተከፈተው የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቶ ለስድስት ወራት ሰልጥኗል። በዚህ መሀል እህቱ ስለታመመች ወደ ሀገር ቤት ሄደ። ጥቂት ቆይቶም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ሥራ ማፈላለግ ጀመረ፡፡

ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ሄዶ በሙዚቀኛነት ሊቀጠር ቢጠይቅም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡ ነገር ግን ልጅነቱን እና ችግሩን አይተው ሻይ የማፍላት ሥራ ሰጡት። በዚህ ሥራ ላይ እያለም የተከሰተውን ሲያስታውስ፣ “ምድጃዋ የኤሌክትሪክ ነበረች፤ ባንድ ቀን ውስጥ ሶስት ጊዜ ኮረንቲ ያዘኝ” ብሎ ነበር። በዚህ ሁኔታ ለስድስት ወር ያህል ከሠራ በኋላ ሥራውን ትቶ በመውጣቱ ለተወሰኑ ወራት ተንከራተተ።

ከብዙ መንከራተት በኋላ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት አካባቢ በሚገኝ አንድ ሻይ ቤት ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ። ሙሉ ቀን ታታሪ እና አመለ ሸጋ በመሆኑ የሻይ ቤቱ ባለቤት ይወዱት እና ይረዱት ነበር። በሻይ ቤቱ እየሠራ በነበረበት ወቅት ሀርሞኒካ የሚጫወት ጓደኛ ስለነበረው ሻይ ቤቱ ቁጭ ይሉና ጓደኛው ሀርሞኒካውን ሲጫወት ሙሉቀን ይዘፍናል።

አንድ ቀን ሙሉቀን እና ጓደኞቹ አብረው ሲጫወቱ ያመሹና አንዱን ጓደኛቸውን ለመሸኘት ሲሄዱ፣ ደጃች ውቤ ሰፈር ሲደርሱ የውቤ በረሃ የምሽት ቤቶች ልዩ ልዩ ቀለማት መብራቶች ሙሉቀንን በጣም ያስደንቁታል። በተለይም ትኩረቱን ስለሳበው አንድ ለየት ያለ ቤት ጓደኛቹን ሲጠይቃቸው ቤቱ ‘ፓትሪስ ሉሙምባ የምሽት ክለብ ይባላል’ ይሉታል።

ወደ ክለቡ ገብቶ ሥራ እንዲሰጡት የክለቡን ባለቤት ወ/ሮ አሰገደች አላምረውን ጠየቃቸው፡፡ ሙዚቃ እንዲፈተን ከቻለ እንደሚቀጥሩት፣ ካልቻለ ደግሞ ሌላ ሥራ እንደሚሰጡት ቃል ገቡለት፡፡

ጥላሁን ገሠሠ እና ዓለማየሁ እሸቴን አስመስሎ ይዘፍን የነበረው ሙሉቀን የተሰጠውን ዕድል ተጠቅሞ በባዶ እግሩና በቁምጣ ሱሪ መድረኩ ላይ ወጥቶ "ለእውነት እሞታለሁ አልሳሳም ለነፍሴ" እና "እንክርዳድ" የተሰኙ የጥላሁን ዘፈኖችን አቀረበ።

እዚያው ምግብ እና ማደሪያ ተሰጥቶት በ90 ብር ወርሃዊ ደመወዝ መሥራት ጀመረ፡፡ ወቅቱን ሲያስታውስም፣ “ዘጠና ብር ስቀጠር ሚልየነር የሆንኩ ነው የመሰለኝ!” ብሎ ነበር።

በፓትሪስ ሉሙምባ የምሽት ክለብ እየተጫወተ እያለ ፖሊስ ኦርኬስትራ ተቀጠረ፡፡ ለፖሊስ ኦርኬስትራ በተቀጠረ በሦስተኛ ቀኑ ከኦርኬስትራው ጋር ወደ መቀሌ ተጉዞ የ“ወይዘሪት ትግራይ” የቁንጅና ውድድር ሲደረግ የጥላሁን ገሰሰን ዘፈኖች ዘፈነ። ታዳሚውም ሙዚቃውን በጣም ወደደው፡፡

ተስፋዬ አበበ(ፋዘር) የደረሷቸውን “እምቧይ ሎሚ መስሎ”፣ “እናቴ ስትወልደኝ መች አማከረችኝ” እና “ልጅነት” የተባሉትን ሦስት ዘፈኖች  በሕዝብ ፊት ይዘፍን ጀመር። በወቅቱ የኦርኬስትራው ድርሰት እና ዝግጅት ኃላፊ የነበሩት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ሙሉቀን ወደ ፖሊስ ኦርኬስትራ የተቀላቀለበትን ሁኔታ ሲያስታውሱ፣ "በምሽት ክለብ ብዙ ቢቆይ ኖሮ ከዕድሜው አንጻር ይበላሽ ነበር፤ እኛ ጋር እንደመጣ ምንም ልምምድ ሳያስፈልገው ነበር ሥራ ውስጥ የገባው" ይላሉ፡፡ በፖሊስ ኦርኬስትራ ውስጥ በሠራቸው ዘፈኖች ታዋቂነትቱ እየጨመረ ሄደ። ጋዜጦቸም “ኮከብ ድምጻዊ ተጫዋች” በማለት ስለሱ መጻፍ ጀመሩ። ከሦስት ዓመታት በኋላ ከፖሊስ ኦርኬስትራ ጋር ተለያየ።

ሰሎሞን ተሰማ የደረሰውን ‘የዘላለም እንቅልፍ’ የሚለውን ግጥም እና አቡበከር አሸኬ የደረሰውን ‘ያላየነው የለም’ የሚሉ ዘፈኖችን በሸክላ አስቀርጾ ለህዝብ ለቀቃቸው፡፡ በዚህም ታዋቂነቱ እየጨመረ መጣ፡፡

በ1972 ዓ.ም ላይ ደግሞ ከዳህላክ ባንድ ጋር ተቀላቅሎ ሠርቷል፡፡ እስከ 1980ዎቹ ድረስ በነበሩት ዓመታት እጅግ ተወዳጅ የሙዚቃ ሥራዎችንም ሠርቷል። ሙሉቀን በተጨማሪም ከእኩዬተርስ ባንድ እና ከኢትዮ ስታር ባንድ ጋር የሙዚቃ ሥራዎቹን ሠርቷል፡፡

ሙዚቃ በቃኝ ብሎ ራሱን ከሙዚቃው ዓለም እስካገለለበት ጊዜ ድረስ ለ17 ዓመታት በርካታ የሙዚቃ ሥራዎችን ለትውልድ አበርክቷል። በተለይ ባሕላዊ ጨዋታዎችን በዘመናዊ ለዛ ሲጫወት ወደር የለሽ ነበር።

ገጣሚ እና ደራሲው ይልማ ገብረ አብ እንደሚለው እንደ ሳንሱር ሙሉቀንን ያማረረው ነገር የለም፡፡ በሳንሱር ስድስት ሥራዎቹ ሲሰረዙበት እንባ አውጥቶ ማልቀሱን ከአበበ መለሰ ጋር እንደተመለከቱት ይልማ ያስታውሳል፡፡

ሙዚቃን አቁሞ ወደ መንፈሳዊ መዝሙር የሄደበት የመጨረሻ ሙዚቃው "ነይ ነይ ወዳጄ ነይ ነይ" የሚለው ዘፈን እንደሆነ የትራምፔት ተጫዋቹ እና ሙዚቃ አቀናባሪው ሻምበል መኮንን መርሻ ያስታውሳሉ፡፡

ከ1980ዎቹ በኋላ ፊቱን ወደ መንፈሳዊ ሥራዎች በማዞር የመዝሙር ሥራዎችን እየሠራ እስከ ህልፈተ ሕይወቱ ድረስ በሀገረ አሜሪካ ኑሮውን አድርጎ ቆይቷል።

ከምንም ተነስቶ ኮከብ ለመሆን የበቃው የቀድሞው ድምጻዊ ሙሉቀን መለሰ በተወለደ በ70 ዓመቱ በአሜሪካን ሀገር አርፏል፡፡ እሱ በአካል ቢያልፍም በሥራዎቹ ግን ህያው ሆኖ ከአድናቂዎቹ ጋር ይኖራል፡፡

ለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top