በጂቡቲ ሰነድ አልባ ሆነው የሚኖሩ ዜጎች ያለባቸውን ችግር ለመፍታት በተለየ መልኩ ይሰራል፡- የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት

13 Days Ago
በጂቡቲ ሰነድ አልባ ሆነው የሚኖሩ ዜጎች ያለባቸውን ችግር ለመፍታት በተለየ መልኩ ይሰራል፡- የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት
በጂቡቲ ሰነድ አልባ ሆነው የሚኖሩ ዜጎች ያለባቸውን ችግር በተሻለ መልኩ ለመፍታት እና የድንበር ኬላ ትብብርን ለማጠናከር በተለየ መልኩ እንደሚሰራ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ገለጸ።
 
በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በሆኑት ሰላማዊት ዳዊት የተመራ የልዑካን ቡድን በጂቡቲ ከተለያዩ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።
 
ምክክሩም በጅቡቲ የሚኖሩ እና ሀገሪቱን እንደመሸጋገሪያ በመጠቀም ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚሄዱ ሰነድ አልባ ዜጎች ያለባቸውን ችግር ለመቅረፍ እና ከኬላ ቁጥጥር ላይ ያለ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
 
ልዑኩ በቆይታው በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የጂቡቲ ኃላፊ እና በጂቡቲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በዘርፉ ባሉ ችግሮች እና በሚወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ዙርያ ጠቃሚ ውይይት ማካሄዱ ተገልጿል።
 
በጅቡቲ ኢምባሲ በተደረገ ውይይት፤ኢትዮጵያውያን በአግባቡ በመለየትና ሰነዳቸውን በማጣራት የጉዞ ሰነድ እንዲዘጋጅላቸው በማድረግ ወደ ሀገር በማስመለስ ስራ ያለው ክፍተት እንዲስተካከል ማስቻልና ይህንንም ወጥ በሆነ መንገድ ለመምራት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል።
 
በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ ጂቡቲ የስደተኞች መተላለፊያ ኮሪደር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ከዜግነት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ስራዎች በከፍተኛ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል።
 
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሯ በበኩላቸው፤ሰነድ አልባ ዜጎችን በተገቢው በመለየትና የጉዞ ሰነዶች በወቅቱ እንዲደርሳቸው እንደሚሰራ ተናግረዋል።
 
ከዜጎች ማጣራት ጋር እና ከድንበር ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ስርዓቱን የማዘመንና ወቅቱን በሚመጥን አግባብ እንዲደራጅ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
 
የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የጂቡቲ ኃላፊ ታኒያ ፓሲፊኮ በዓለም አስከፊ ሁኔታን እየተጋፈጡ ካሉ ፍልሰተኞች ኢትዮጵያውያን ቀዳሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
 
ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ ተቋማቸው እያከናወነ ያለውን ጥረት ጠቅሰው፤ በቀጣይም ከፍልሰተኞች ሰነድና የማስመለስ ስራ ጋር በተያያዘ በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
 
ወ/ሮ ሰላማዊት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ድርጅቱ እያከናወነ ላለው በጎ ተግባር ምስጋና በማቅረብ ፤ቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች የዓለም አቀፉ ድርጅት ድጋፍ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።
 
በዋና ዳይሬክተሯ የተመራው ልዑክ በጂቡቲ ጊዚያዊ መጠለያ የሚገኙ ዜጎችን በአካል ተገኝቶ የተመለከተ ሲሆን በነፃ የንግድ ቀጠና እና ወደብ አከባቢ ያሉ እንቅስቃሴዎችንም ጎብኝቷል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top