በበረሃ ውስጥ የሚያበራው የበረሃው ገነት

13 Days Ago
በበረሃ ውስጥ የሚያበራው የበረሃው ገነት

ለብዙዎች በረሃማ ስፍራ ምንም የሌለበት ምድረ በዳ ወይም አሸዋን ማሰብ ይቀናል።  በእርግጥም ውኃ አጠር አካባቢ እንደመሆኑ ሕይወት ከባድ እንደሆነ መገመት አይከብድም::

ወደ ኢራን ስናቀና የምናገኘው በረሃ ግን በውስጡ "ገነትን" ይዟል ይለናል ኦዲቲ ሴንትራል የመረጃ ምንጭ። ይህ ስፍራ የኢራን ሻዝዴህ የአትክልት ስፍራ፣ የልዑል ገነት በመባል ይታወቃል::

በሚያስደንቅ ሁኔታ በአረንጓዴ ተክሎች የተሞላ ለምለም የአትክልት ስፍራ ሲሆን ይህ ደረቅ በረሃ በምንጭ ውኃ የተከበበም ነው።

በከርማን ግዛት ከማሃን ከተማ 6 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሻዝዴህ የአትክልት ስፍራ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በካጃር ሥርወ መንግሥት የተገነባ ታሪካዊ የፋርስ አትክልት ስፍራ እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ።

አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ይህ ስፍራ በድንጋይ ግድግዳዎች የተከበበ ሲሆን  አጥር ሆኖ የከበበው ድንጋይም በውስጡ ያለውን አረንጓዴ የተዋበ የአትክልት ስፍራ በዙሪያው ካለው ከባድ በረሃ ይከላከለዋል ተብሎ ይታሰባል።  

በአየር ላይ በካሜራ ዕይታ  ሻዝዴህ የአትክልት ስፍራ ያዩት ሰዎች  በበረሃማ ባሕር መካከል የሚገኝ እንግዳ ተቀባይ ወንዝ ይመስላል ይሉታል።

እነዚህ የአየር ላይ ፎቶዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በየዓመቱ ወደዚህ ቦታ እንዲመጡም ምክንያት ሆኗል።

በዚህ ከባድ በረሃ ውስጥ የሚገኘውን ይህንን አትክልት ስፍራ  የሚመግቡት ከመሬት በታች ካለ የውኃ ጉድጓድ ውስጥ የሚቀርቡ አምስት የውኃ ምንጮች ናቸው።

ከአውሮፓውያኑ 2011 ጀምሮ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ሻዝዴህ የአትክልት ስፍራ አሁን ላይ ከመላው ዓለም ለሚመጡ  ጎብኚዎች ታዋቂ እና ተመራጭ መዳረሻ ነው።

 5.5 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ስፍራ አረንጓዴ ተክሎች፣ የውኃ ምንጮች እና ኩሬዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የሥነ-ሕንፃ ስራዎችን በውስጡ ይዟል።

"የበረሃው ገነት"፣ "በበረሃ መካከል የሚያበራ አልማዝ" ተብሎም በብዙዎች ስም ወጥቶለታል።

ይህ ውብ የበረሃ የአትክልት ስፍራ ከታሰበ በረሃማ የሚባሉ ስፍራዎችን ማልማት እንደሚቻል ማሳያም ነው።

 

 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top