እየሩስ አባቷ ማን ነው?

13 Days Ago
እየሩስ አባቷ ማን ነው?

በሀገራችን የፊልም ታሪክ ከታወቁ ፊልሞች መሐል "ሂሩት አባቷ ማነው!?" የሚል ርዕስ ያለው ፊልም ይጠቀሳል።

በዚህ ፅሁፍ ላይ "እየሩስ አባቷ ማነው?" የሚለውን ጥያቄ አንስተን ምላሹን ለማግኘት በመደበኛው የተለመደ ሂደት አንድ ልጅ አባቱ ወይም ጥቅምና መብት ያላቸው ሰዎች ልጅነቱን ሳያውቁ ሲቀሩ አባትነትን በሕግ ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ሂደቶችንና ማስረጃዎችን በተመለከተ እስከ ፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሰ ክርክርና ውሳኔን እንቃኛለን።

እየሩስና ፊታውራሪ

ፊት አውራሪ ክፍሌ ሲሞቱ እየሩስ ፊትአውራሪ በ1971ዓ.ም ከእናቴ ጋር ከጋብቻ ውጪ በነበራቸው ግንኙነት ወልደውኛል በየወሩ (ሁለት መቶ ብር) የቀለብ ገንዘብ ለእናቴ እየሰጡ ያሳድጉኝ ስለነበር ፊት አውራሪ አባቴ መሆናቸው ይታወቅልኝ ስትል ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረበች።

"እንዴት ተደርጎ" የሚሉት የፊት አውራሪ ባለቤት ወ/ሮ ዘውዲቱም፤ ጠበቃ ቀጥረው "እየሩስ የፊታውራሪ ልጅ አይደለችም። ከፊታውራሪ ጋር እስኪሞቱ ድረስ የአባት እና ልጅ ግንኙነት አልነበራቸውም።" ሲሉ የእየሩስ አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግ ጠየቁ፡፡

ፍርድ ቤቱ ምስክሮችን ሰማ። የእየሩስ ወላጅ እናት በምስክርነት ቀርበው “በሶማሌ ጦርነት ጊዜ ከአንድ የውጪ ዜጋ ጋር በፊታውራሪ ቤት ተከራይቼ እኖር ነበር፡፡ ፈረንጁ ወደ ሀገሩ ሲሄድ ፊታውራሪ ልጅ ውለጂልኝ ቤት ተከራይቼ አስቀምጥሻለሁ እንዳሏቸው እና ልጅ እንደወለዱላቸው” የእየሩስ እናት መሰከሩ። 

ሌላኛው ምስክር በበኩላቸው፤ ፊታውራሪ እና የእየሩስ እናት ከ1969-1980 ዓ.ም በሰገነት ሆቴል ወጣ ገባ ሲሉ እንደሚያውቋቸው መሰከሩ፤ ሌሎችም ምስክሮች ተሰሙ፡፡

እስቲ የፍርድ ቤቶቹን ውሳኔ ከማንበባችሁ በፊት በቀረበላችሁ መረጃና ባላችሁ የሕግ ግንዛቤ ላይ በመመስረት ግምታችሁን በሀሳብ መስጫ ሳጥኑ ውስጥ አሳውቁን። ፊታውራሪ የእየሩስ ወላጅ አባት ናቸው? ለምን?

ፍርድ ቤቶቹ በየደረጃው ምን ወሰኑ

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤት “እየሩስን እና ፊታውራሪን አባት እና ልጅ የሚያስብል ነገር አላገኘሁም።” ብሎ ወሰነና የእየሩስን የፊታውራሪ ልጅነቷን የማረጋገጥ አቤቱታ ውድቅ አደረገው።

ጉዳዩን በእየሩስ ይግባኝ ባይነት በይግባኝ የተመለከተው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ደግሞ "የምስክሮች ቃል ውስጥ ልዩነት የታየው ጊዜው በመርዘሙ ነው። እየሩስ የፊታውራሪ ልጅ ናት ሲል ወሰነ፡፡

በወ/ሮ ዘውዲቱ  በኩል ይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የከፍተኛውን ፍ/ቤት ውሳኔው አፀናው።

ጉዳዩ በወ/ሮ ዘውዲቱ አመልካችነት ( ሴትየዋ የፊታውራሪ ሚስት መሰሉኝ፤ ውሳኔው  ላይ ማንነታቸው አልተጠቀሰም) ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀረበ፡፡

በተሻሻለው የፌደራሉ የቤተሰብ ሕጋችን አባትነትን ማወቂያ ድንጋጌዎች መሰረት እየሩስ የፊታውራሪ ልጅ ነች አይደለችም የሚለውን ነጥብ ይዞ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል ፡፡

የሰበርን ውሳኔ ከማየታችን በፊት ሕጉ የሚለውን እንመልከት፡፡

በ1992 ዓ.ም የወጣው የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እናትን በአንቀጽ 120 ላይ ልጁን በመውለዷ ብቻ እናትነቷ እንደሚታወቅ ይደነግጋል።

አንድ ሰው የአንድ ሕፃን አባት ነው ለመባል ፡-

- ሕፃኑ በሚፀነስበት ወይም በሚወለድበት ጊዜ የእናትየው ባል ከነበረ ወይም ጋብቻ ባይፈጽሙም ከእናቱ ጋር እንደባልና ሚስት አብሮ ይኖር የነበረን ሰው ሕጉ አባት ነህ ብሎ ይገምተዋል።

ለዚህ ግምት ተግባራዊነትም አንድ ልጅ ተጸነሰ የሚባለው ከመወለዱ ከ300 ቀናት በፊት ሲሆን ጋብቻ ከተፈጸመ 180 ቀናት በኋላ ወይም ጋብቻው በፈረሰ 300 ቀናት ውስጥ የተወለደ ልጅ በተ/የፌ/የቤ/ሕ/አ 128 መሰረት በጋብቻ ውስጥ እንደተወለደ ይቆጠራል።

- ልጁ በጋብቻ ውስጥ ወይም እንደ ባልና ሚስት አብረው ከሚኖሩ ወላጆች ካልተወለደ ደግሞ በ/የፌ/የቤ/ሕ/አ 132 አባትየው ልጄ ነው ሲል የተወለደ ወይም የተጸነሰ ልጅን በመቀበሉ አባትነት ይታወቃል። ሆኖም በአንቀጽ 136 መሰረት የልጁ እናት ያላመነችለት ሰው አባት ነኝ ቢልም ሕግ አይቀበለውም።

በሕጉ ግምት ወይም አባትየው በሰጠው እውቅና አባትየው ካልታወቀ በተ/የፌ/የቤ/ሕ/አ 143 መሰረት በፍርድ ውሳኔ አባትነት የሚታወቀው በሚከተሉት ምክንያቶች መሆኑን የተሻሻለው የፌደራሉ የቤተሰብ ሕግ ይደነግጋል።

ልጁ የተፀነሰው እናቲቱ በመደፈሯ ወይም በመጠለፏ ከሆነ፣ በተንኮንል፣ በማታለል፣ በጋብቻ የተስፋ ቃል ወይም በማሳት ከሆነ፤ አባት የፃፋቸው የማያሻሙ ልጅነትን የሚያረጋግጡ ጽሁፎች ሲኖሩ፤ በሕግ ባይታወቅም እናትና አባት ቀጣይነት ያለው የግብረስጋ ግንኙነት ካደረጉ ወይም አባት የተባለው ሰው እንደ አባት ልጁን ካሳደገ አባትነትን በፍርድ ቤት ውሳኔ ማረጋገጥ እንደሚቻል ሕጉ ደንግጓል።

የአንድ ሰው አባትነት ታውቆ በአባት እና በልጅ መሐል ያሉ ሕጋዊ መብትና ግዴታዎች የሚፈጠሩት ከላይ በጠቀስናቸው አንቀፆች መሰረት ነው።

 እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ የሄደው የፊት አውራሪ ክፍሌ ልጅ ነኝ ባይዋ እየሩስ እና የጣልቃ ገብ ወ/ሮ ዘውዲቱ ክርክር (በነገራችን ላይ የተከራካሪዎችን እውነተኛ  ስም ቀይሬዋለው) በሰ/መ/ቁ/ 44612 ጥቅምት 10 ቀን 2002 ዓ.ም ውሳኔ ተሰጥቶበታል።

 ሰበር ሰሚ ችሎቱ ፊት አውራሪ ክፍሌ በሕግ ግምትም ሆነ እየሩስን ልጄ ብለው በማወቃቸው አባቷ ናቸው የሚያስብል ማስረጃ ስላልቀረበ የመ/ደ/ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ የከ/ፍ/ቤት እና የጠ/ፍ/ቤት መሻራቸው አለአግባብ ነው። እየሩስ የፊትአውራሪ ክፍሌ ልጅ አይደለችም።"ብሎ ወስኗል።

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top