"በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በማዕድን ሀብት ልማት ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው"- ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

12 Days Ago
"በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በማዕድን ሀብት ልማት ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው"- ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በማዕድን ሀብት ልማት ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
 
በክልሉ የማዕድን ልማት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ የማዕድን ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በተገኙበት በአሶሳ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
 
በንቅናቄ መድረኩ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በክልሉ 238 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን ገልጸዋል፡፡
 
ይሁን እንጂ ክልሉ ካለው እምቅ የማዕድን ሀብት አንጻር ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ ምርት አነስተኛ በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡
 
በተለይ ሕገ ወጥ የወርቅ አዘዋዋሪዎች እና አምራቾች ከድርጊታቸው በመቆጠብ እና ሕጋዊ አሰራርን በመከተል ለዘርፉ ዕድገት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ ሕጋዊ አሠራርን በማይከተሉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አስገንዝበዋል፡፡
 
የማዕድን ሚኒስትር ዴዔታው አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ በበኩላቸው፤ ክልሉ ያለውን የማዕድን ሀብት በአግባቡ በማልማት ለክልሉ ማህበረሰብ ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ እንድኖረው ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ዕገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡
 
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል መሀመድ፤ በክልሉ ወርቅ፣ እምነበረድ፣ የድንጋይ ከሰል ግራናይት እና የመሳሰሉ ማዕድናት እንደሚገኙ ገልጸው፤ በዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር ቢሮው እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
 
በንቅናቄ መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት አምራች ማህበራትና ግለሰቦች የተገኙ ሲሆን የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ ማህበራት ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡
 
በጀማል አህመድ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top