ጸሎተ ሐሙስ

1 Mon Ago
ጸሎተ ሐሙስ

ጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ ቁርባንን ከምሥጢረ ጸሎት ጋር አዋሕዶ ያሳየበት ዕለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ እና ለአርዓያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡

 ትሕትና፣ ፍቅር፣ መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳት እና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ‘ሕጽበተ ሐሙስ’ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡

በአንደኛው ሰዓተ ሌሊት ሐሙስ ምሽት ኢየሱስ ክርስቶስ ማበሻ ጨርቅ አንስቶ ወገቡን በመታጠቅ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጥብ ዘንድ በጴጥሮስ ጀመረ፤ ጴጥሮስ ግን "እኔ ባንተ ልታጠብ አይገባኝም አለ"፤ ኢየሱስም መልሶ "እውነት እውነት እልሃለሁ፤ እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም" አለው፡፡ ሌሎቹንም ሐዋርያት አጠባቸው፤ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳንም እግሩን አጠበው፡፡

ኢየሱስ የይሁዳን እግር ያጠበው አሳልፎ እንደሚሰጠው ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን ፍቅርን ሲያስተምረው እና ለንስሐ ጊዜ ሲሰጠው እንደሆነ፤ ሰዎችም ለሚወዱአቸው ብቻ ሳይሆን ለሚጠሉአቸውም ጭምር በጎ ማድረግ እንደሚገባ በምሳሌ ሲያስተምር እንደሆነ የቤተክርስቲያኒቱ አስተምሕሮ ያሳያል፡፡

የሐዋርያትንም እግር አጥቦ "እናንተም እንዲህ አድርጉ" ብሎ ትህትናን አስተማራቸው፡፡ ይህም እሱ አምላክ ሆኖ ሳለ፤ ዝቅ ብሎ የሐዋሪያቱን እግር እንዳጠበው የሐይማኖት አባቶች እና የህዝብ መሪዎችም ዝቅ ብለው ህዝብን ማገልገል እንደሚገባቸው ለማሳየት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል እሱ በትህትና ዝቅ ብሎ እግራቸውን ያጠበው በትዕቢት ወደ ዓለም የገባውን ሞት ለመሻር እንደሆንም ይነገራል፡፡

በሁለተኛው ሰዓተ ሌሊት ምሽት ኢየሱሰስ ክርስቶስ ሕብስቱን ባርኮ ለሐዋሪያቱ ሰጣቸው፤ "ይህ ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ" ወይኑንም ባርኮ፣ "ይህ ደሜ ነው እንካችሁ ጠጡ" ብሎ በመስጠት ሚስጥረ ቁርባንን አስጀመረ፡፡ ማዕዱንም "እውነት እውነት እላችኋለሁ! ከእናንተ መካከል አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል" በማለት ይሁዳ ጸሐፍት ፈሪሳውያን እና ካህናት ጋር ተባብሮ አሳልፎ እንደሚሰጠው ተናገረ፡፡ ይሁዳም አሳልፎ የሚሰጥበትን ዋጋ ሊነጋገር ፈጥኖ ወጥቶ ወደ አይሁዳውያን ሔደ፡፡ 

ከሦስተኛው ሰዓተ ሌሊት እስከ ሌሊት አምስት ሰዓት ድረስ ደቀ መዛሙርቱን ሲመክራቸው፣ የመንፈስ ቅዱስንም መምጣት አብዝቶ ሲነግራቸው፣ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ እርሱ ከአባቱ ጋር አንድ እንደሆነም ነገራቸው፡፡ ለብቻው ፈቀቅ ብሎ እየሰገደ ጸለየ፤ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመለስ ተኝተው ስላገኛቸው ጴጥሮስን "አንድ ሰዓት ያህል እንኳን ከእኔ ጋር መትጋት አቃታችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ" ብሎት ሄደ፡፡

እኩለ ሌሊት በስድስተኛው ሰዓት አትክልት ወደ አለበት ስፍራ ወደ ቄድሮስ ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ ይሁዳም ይህችን ስፍራ ቀድሞ ኢየሱስ ይመጣባት ስለነበር ያውቃት ነበርና ፋና ጋሻ ጦርም የያዙትን አስከትሎ መጣ፡፡ ይሁዳም ወደርሱ ቀርቦ፤ "መምህር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን" ብሎ ሳመው፤ ይህ መሳም ለአይሁድ ጥቆማ ወይም ምልክት ነበር፡፡ 

ኢየሱስንም ከበውት ወደ ሽማግሌዎች እና የካህናት አለቃ ቀያፋ ወዳለበት ወሰዱት፤ በዚያም እንደ አመጸኛ ከሰሱት፡፡ ከአርብ ማለዳ ጀምሮም አሰቃዩት፡፡

ዕለቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ቁርባኑን ያሳየበት ስለሆነ ከሰሙነ ሕማማት ዕለታት በተለየ መልኩ ተቀድሶ ቁርባን የሚከናወነወበትም ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ ካከናወናቸው የሥርዓተ ተግባራት በተጨማሪም በዕለቱ ትውፊታዊ ሥርዓትን በጠበቀ ሁኔታ “ጉልባን” የተባለው ምግብ ይበላል።

ጉልባን የባቄላ ክክ እና ከስንዴ አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚባላ ንፍሮ ሲሆን፤ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታን የሚያመለክት ነው፡፡ 

ያን ጊዜ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መብላት፣ ንፍሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ፣ ተግባራቸው ነበርና ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት የእስራኤል ከግብጽ መውጣት ይታወሳል፡፡

ጉልባኑ አንዲሁም ቂጣው ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፤ ይህም ጨው ውኃ የሚያስጠማ በመሆኑ የኢየሱስ ክርስቶስን መጠማት እንዲያስታውስ ነው፡፡ ይህ ትውፊታዊ ሥርዓት ከእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም አብዛኛዎቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ነው ሥርዓቱ ዛሬም የሚታሰበው፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top