የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ለ1 ሺህ 455 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

15 ቀን በፊት
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ለ1 ሺህ 455 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ1 ሺህ 455 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ። 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፥ መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ የክልሉ መንግሥት የይቅርታ አዋጁን መስፈርት ላሟሉ 1 ሺህ 455 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታውቀዋል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፥ ይቅርታ የተደረገላቸው የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ሥነ-ምግባር ያሳዩ እና በሕግ የተደነገገውን የይቅርታ መስፈርት ማሟላታቸው በክልሉ የይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ የቀረቡ ናቸው። 

በዚሁ መሰረት የይቅርታው ተጠቃሚዎች ይቅርታ በማያስከለክሉ ወንጀሎች ተሳትፈው በማረሚያ ቤት የቆዩ፤ የጤና ችግር ያለባቸው፤ ዕድሜያቸው የገፋ እና ከሕጻናት ጋር አብረው የታሰሩ እንዲሁም ከተፈረደባቸው አንድ ሦሥተኛ እና ከግማሽ በላይ የፍርድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። 

ይቅርታው ከተደረገላቸው 1 ሺህ 455 የሕግ ታራሚዎች መካከል1 ሺህ 435ቱ ከእስር የሚፈቱ ሲሆን፤ ቀሪ 20 ታራሚዎች የእስራት ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው ገልጸዋል። 

የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ የሕግ ታራሚዎች የይቅርታን እሴት ተላብሰው ሰላም ወዳድ፣ ለሕግ ተገዥና አምራች ዜጋ በመሆን በተለያዩ የልማት ስራዎች ህብረተሰቡን ማገልገል እንደሚገባቸው ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል። 

ህብረተሰቡም በይቅርታ የተለቀቁት የሕግ ታራሚዎች በፈፀሙት ጥፋት የተፀፀቱና በአግባቡ ታርመው የወጡ መሆኑን በመረዳት መልካምና አምራች ዜጋ ይሆኑ ዘንድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ከርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top