ሙያዊ ጥፋት እና ሕክምና

1 Mon Ago
ሙያዊ ጥፋት እና ሕክምና

አይበለውና ላጋጠማችሁ የራስ ወይም የቅርብ ቤተሰብ የጤና ዕክል ወደ ሐኪም ዘንድ ሄዳችሁ በሙያዊ ጥፋት ሌላ ያልታሰበ ጉዳት ቢደርስባችሁ ምን ታደርጋላችሁ? ሕጎቻችንስ በጉዳዩ ላይ ምን ይላሉ?

በአገራችን የሕክምና ጉዳትን የሚመለከቱ ክሶች ወደ ፍርድ ቤቶች እንደማይመጡ ይነገራል። ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዓመት የቀረቡ የሕክምና ጉዳት ክሶች በጣት የሚቆጠሩ እንደሆኑ ሀብታሙ ስማቸው የተባሉ የሕግ ባለሙያ በሕግ ለማስተርስ ዲግሪ መመረቂያ የሰሩት ጥናት ያመለክታል።

የተለያዩ ጥናቶቸ እንሚያሳዩት በታዳጊ አገራት ከአስር ታካሚዎች አንዱ በሕክምና ላይ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። ከጤና ክብካቤ ጋር በተያያዘ በታዳጊ አገራት፣ ካደጉ አገራት በ20 እጥፍ ለኢንፌክሽን ጉዳት የመጋለጥ ዕድል አለ። በሕግ ባለሙያው ሀብታሙ ስማቸው ግምት፥ አገራችን ካለችበት ዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ አንፃር የሕክምና ስህተት ጉዳቱ የባሰ ሊሆን ይችላል።

በፍትሐ ብሔር ሕጋችን በቁጥር̣ 2639 ድንጋጌ መሰረት፥ የሕክምና ወይም የሆስፒታል አገልግሎት ውል ሐኪሙ ወይም ሆስፒታሉ ታካሚውን አክሞ በተቻለው መጠን በመልካም ጤና እንዲቆይ ወይም እንዲድን የሚገባው ውል ነው።

ሐኪሙ ወይም የጤና ባለሙያው የሚፈፅመው ሙያዊ ጥፋት ታካሚው ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት፣ በሕክምና ሙያው የሚጠበቅበትን ሕክምና ባለማድረጉ ወይም ሕክምናውን ሲሰጥ ላዳረሰው ጉዳት፣ ለሕክምና የተቀበለውን ሰው በቂ ባልሆነ ምክንያት ምትክ ሳይተካ በመተው ለሚደርሰው ጉዳት ካሳ የመክፈል ኃላፊነት አለበት።

ሆስፒታሎች ደግሞ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2651 መሰረት ሐኪሞቻቸው ወይም የሐኪሙ ረዳት ሠራተኞች ላደረሱት ጉዳት ኃላፊ ናቸው። ሆስፒታሉ የካሳ ተጠያቂነት የሚኖርበት ሠራተኛው ታካሚው ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት የአሠሪነት ወይም ሕክምናውን እንዲያደርግ ሐኪሙን በመወከሉ የወካይነት የሕግ ኃላፊነት ስላለበት ነው። በሆስፒታሉ ወይም በጤና ተቋሙ እና በታካሚው መካከል የሕክምና ውል ከሌለ ደግሞ ተቋሙ ከውል ውጭ በሚደርስ የጉዳት ካሳ ኃላፊነት ሊጠየቅ ይችላል።

ራሳቸውን ችለው በጤና ተቋሙ ውስጥ የሚሰሩ የቅጥር ወይም የውክልና ውል የሌላቸው የጤና ባለሙያዎች ለሚያርሱት ጉዳት ግን በሀገራችን ሆስፒታሉንም ተጠያቂ የሚያደርግ የሕግ መሰረት አለመኖሩን  አቶ ሀብታሙ በጥናቱ ላይ አስምረውበታል።

ሐኪሙ በቸልተኝነት ወይም በስህተት ተገቢውን ሕክምና ባለመስጠት ታካሚው ላይ ጉዳት አድርሷል የሚባለው ሙያው የሚጠይቀውን እውቀትና ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረግ ታካሚው ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ነው። ሐኪሙ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል ወይስ አልሰጠም? የሚለውን ሙያዊ ጥያቄ ለመመለስ የሕክምና ባለሙያዎች ማህበር የሚሰጠውን ሙያዊ አስተያየት ፍርድ ቤቶች የሕክምና ጉዳት ሙግቶችን ለመወሰን በማስረጃነት ይጠቀሙበታል። ለማሳያነት በፍርድ ቤቶቻችን የተዳኙ ሁለት የሕክምና ጉዳት ክሶችን እናንሳ።

 

ሰናይትና ሜሪስቶፕስ

ሰናይት የወሊድ መቆጣጠሪያ ሕክምና ለማግኘት ወደ ሜሪስቶፕስ አመራች። ተገቢው ምርመራ ተደርጎላት ኖርፕላንት የወሊድ መከላከያ ከንዷ ላይ ተቀበረላት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ክንዷ ላይ ሕመም ስላስቸገራት ተመልሳ ወደ ክሊኒኩ ስትሄድ፣ የጤና ባለሙያው ምርመራ አድርጎላት ኖርፕላንቱ መውጣት እንዳለበት ወሰነና መልሶ አወጣላት።

ሆኖም የሚሰማት ሕመም ተባብሶ የጀርባ ሕመምና የጡት እብጠት ስላጋጠማት ሰናይት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሜሪስቶፕስ ላደረሰባት የሕክምና ጉዳት ኃላፊ እንዲሆን፣ በጉዳቱ ምክንያት በውጪ አገር ለመታከምና ጠቅላላ ወጪዋን 694, 918 ብር የጉዳት ካሳ እንዲከፍላት ክስ መሰረተች።

ፍርድ ቤቱ ከሳሽ ሰናይትን እና ተከሳሽ ሜሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ክሊኒክን አከራከረ። በክርክሩ የተከሳሹ የጤና ባለሙያ የሕክምና ስህተት መፈጸሙን አረጋግጫለሁ። ከሳሽ ሰናይት በጉዳቱ የተነሳ ላወጣችው ወጪ የ300 ሺህ ብር ካሳ ሜሪስቶፕስ ይክፈላት ሲል ወሰነላት።

ሁለቱም ተሟጋቾች ይግባኝ ጠየቁ። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሜሪስቶፕስን ይግባኝ ውድቅ አድርጎ የሰናይትን ይግባኝ በመቀበል  300 ሺህ ብር ብቻ ሳይሆን፤ የጠየቀቸው የካሳ መጠን በሙሉ ተገቢ ነው ብሎ የስር ፍ/ቤት ውሳኔን በማሻሻል 694, 918 ብር ካሳ ሜሪስቶፕስ ለሰናይት እንዲከፍላት ወሰነ። ሜሪስቶፕስ ውሳኔውን ለማሻር ወደ ሰበር ቢሄድም አልተሳካለትም።

 

አብርሃምና ጥቁር አንበሳ ከአራት ዶክተሮቹ ጋር

አብርሃም የተሽከርካሪ አደጋ ደርሶበት ግራ እግሩ ይሰበርና ጥቁር አንበሳ ለሕክምና ይገባል። ሆኖም አራቱ የጥቁር አንበሳ ዶክተሮች ባደረጉለት የተሳሳተ ሕክምና የተጎዳውን የግራ እግሩን ትተው ደህነኛው የቀኝ እግሩ ላይ ቀዶ ጥገና በማድረጋቸው 65% የአካል ጉዳት ስለደረሰበት አራቱን ዶክተሮችና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ለደረሰበት ጉዳት 2,550,752 ብር የጉዳት ካሳ እንዲከፍሉት ከሰሳቸው።

አራቱ ዶክተሮች ቀኝ እግሩ ላይ የቲቢ ምርመራ ውጤት ሰላገኘን ነው የቀዶ ሕክምናውን ያደረግነው፤ ስለዚህ ልንጠየቅ አይገባም ሲሉ ተከራከሩ። ሆስፒታሉ በበኩሉ፥ የመንግሥት ተቋም ሰለሆነ ዶክተሮቹ በግል ለሠሩት ጥፋት ልጠየቅ አይገባም አለ።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ አራቱ ዶክተሮችና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አብርሃም ላይ ለደረሰው የሕክምና ጉዳት ኃላፊ ናቸው ሲል ውሳኔ ሰጥቷል። ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም ውሳኔውን አፅንቶታል።

 

ሙያዊ ግዴታን የሚመለከቱ የወንጀል ኃላፊነቶች

በሙያዊ ችልተኝነት የሞት ጉዳት ያደረሰ የሕክምና ባለሙያ በወንጀል ሕግ አንቀፅ 543 (2) መሰረት ከ1 ዓመት እስከ 5 ዓመት እስር እና ከ3 ሺህ እስከ 6 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል። የሕክምና ባለሙያው የሞት ጉዳት ያደረሰው ግልፅ ደምብ ወይም መመሪያ ተላልፎ ከሆነ፣ ወይም ከሁለት በላይ ሰዎችን ከገደለ፣ ወይም ጥፋቱን የፈፀመው የሚያደነዝዝ ወይም የሚያሰክር ንጥረ ነገር ወስዶ ከሆነ፤ ቅጣቱ ከ 5 ዓመት እስከ 15 ዓመት እስር እና ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ነው።

በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 559 (2) መሰረት የሌላውን ሰው ጤና የመጠበቅ የሙያ ግዴታ እያለበት በቸልተኝነት የአካል ጉዳት ያደረሰ የጤና ባለሙያ ከ6 ወር በማያንስ ቀላል እስራት እና ከ1 ሺህ ብር በማያንስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል።

ለመሆኑ በኛ አገር ከሙያዊ ጥፋት በተለይም ከሕክምና ስህተት ጋር በተያያዘ ምን አጋጠማችሁ፣ ምን ታዘባችሁ? ባለሙያዎችስ ምን ትላላችሁ? ሃሳባችሁን አካፍሉንና እንወያይበት።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top